You are currently viewing

  • Post comments:0 Comments

ብልጽግና የለውጡን ሀዲድ ተከትሎ ወደ ብልጽግና ማማ መምዘግዘግ ከጀመረ የፊታችን መጋቢት 24 ሶስት ዓመት ይሆነዋል፡፡ በእነዚህ ዓመታት በበርካታ ችግሮች የተተበተበውን የአገራችንን የዴሞክራሲ መጫወቻ ሜዳና የፖለቲካ ምኅዳሩ በማስፋት በኩል፣ ከፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር ግንኙነትና ተቀራርቦ በጋራ ጉዳዮች ላይ መመካከር፣ የሴቶች ፖለቲካዊ ተሳትፎና ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት በማሳደግ በኩል እንዲሁም መሰረታዊ የሆነውን የተቋማት ግንባታ ላይ ያመጣው ለውጥ ከብዙ በጥቂቱ የሚገለጽ ነው፡፡

ያልተፈቱና ውስብስብ የሆኑ ችግሮችን ደግሞ በዘላቂነት ለማስወገድ ያላሰለሰ ጥረት እያደረገ ይገኛል፡፡ የፖለቲካ አንዱ መገለጫ ሰጥቶ የመቀበል መርህ እንደመሆኑ መጠን በተቻለ መጠን ከግጭትና ካላስፈላጊ ትንቅንቅ ወጥቶ የዴሞክራሲን ቡቃያ እንዲያብብ ማድረግ የሥልጣኔ ምልክት ነው፡፡

ብልጽግና መጪውን ሀገራዊ ምርጫ ነጻ፣ፍጹም ዴሞክራሲያዊና ተዓማኒነት ያለው ለማድረግ ብሎም ታሪካዊ ኃላፊነቱን ለመወጣት ተዘጅቷል፡፡ ለዚህ ደግሞ የሕዝብን መብት ማክበርና ተሳታፊነቱን ማረጋገጥ ይገባል ብሎ ያምናል ፓርቲው፡፡እርግጥ ነው እንደ ሀገር በርካታ ያልተፈቱ ውስጣዊም ሆኑ ውጫዊ ጋሬጣዎች እንዳሉ ይታወቃል፤ሆኖም ግን በአስቸጋሪ ሁኔታዎች ውስጥ ተሁኖም ለሰላማዊ ፖለቲካ እንቅስቃሴ ስኬት የድርሻን መወጣት ካልተቻለ ለአገር አሳሳቢ መሆኑ አያጠያይቅም፡፡

ምርጫና ዴሞክራሲ የማይነጣጠሉ አንድ አካል በሆኑበት በዚህ ዘመን ለዴሞክራሲ ሲባል ምርጫ በሕዝብ በጎ ፈቃድ ሊከናወን ይገባል፡፡ ይህ ተግባራዊ ይሆን ዘንድም ሁሉም ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች ኃላፊነት ሊወጡ ይገባል፡፡ በማንኛውም ዴሞክራሲያዊ አገር እንደሚደረገው ሆነ በበርካታ ታዳጊ አገሮች የመንግሥት ሥልጣን መያዝ የሚቻለው በምርጫ ብቻ ነው፡፡

ምርጫ በሰላማዊና በዴሞክራሲያዊ መንገድ የሚከናወነው ወሳኙ ሕዝብ ድምፁን በነፃነት ሲሰጥ ብቻ ነው፡፡ ሕዝቡ ይህንን ነፃነቱን ተጠቅሞ ለምርጫ እንዲወጣ ማድረግ የሚቻለው ሁሉም ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች በዴሞክራሲያዊ መንገድ ሲንቀሳቀሱ ነው፡፡ ይህ ማለት ምርጫው ፍጹም ሰላማዊ በሆነ መንገድ እንዲጠናቀቅ ሀላፊነታቸውን መወጣት አለባቸው እንዲሁም ሕዝቡ መብቱ ተከብሮ የምርጫ ተዋናይ እንዲሆን የፖለቲካ ፓርቲዎች ጥረት ማድረግ የግድ ይላቸዋል፤ምክንያቱም ያለ ሕዝብ ተሳትፎ ዴሞክራሲያዊ ምርጫ አይኖርም!

ምላሽ ይስጡ