You are currently viewing የታላቁ ህዳሴ ግድብ እንደ አድዋ /በሚራክል እውነቱ/

የታላቁ ህዳሴ ግድብ እንደ አድዋ /በሚራክል እውነቱ/

  • Post comments:0 Comments


78% የደረሰውን ታላቁን የህዳሴ ግድብን በፍጥነት ማጠናቀቅ አዲሱን የግብፅ ቅኝ ግዛት መንፈስ ለዘለቄታው ምላሽ ነው። የፕሮጀክቱ ግንባታ መጠናቀቅ ጥቅሙ ለኢትዮጵያዊያን ብቻ አይደለም፤ይልቁንም ጎረቤት ሀገር ሱዳንን ጨምሮ ሌሎች የጎረቤት ሀገራት የኤልክትሪክ ሀይል ተጠቃሚዎች ያደርጋቸዋል ። አንዳንዶቹን ሀገራት ደግሞ በየዓመቱ ይደርስባቸው ከነበረው የጎርፍ አደጋ የሚታደጋቸው ይሆናል፡፡


የአድዋ ድል ለመላው ጥቁር ህዝቦች እና አፍሪካዊያን ወንድሞቻችን አይቻል የሚመልሰለውን የቅኝ ግዛት ቀንበር መስበሪያ ርዕዮት ዓለም ነበር ፓን ኢትዮጵያኒዝም ወደ በኋላ ላይ ፓን አፍሪካኒዝም የተሸጋገረው።


አሁንም የህዳሴው ግድብ ከተጠናቀቀ በሁሉም የናይል ተፋሰስ አባል ሀገራት የግብፅን ሴራ እንዴት መቋቋምና ውጤት ላይ መድረስ እንደሚቻል ትምህርት የሚወስዱበት ታሪክ ቀያሪ ምዕራፍ ተደርጎ ይወሰዳል፡፡

ኢትዮጵያዊያን እንደ ዓይን ብሌናቸውን የሚመለከቱት ታላቁ የህዳሴ ግድቡ ለአፍሪካዊያን ሌላም የምጣኔ ሀብት ሞዴል ይዞ የሚመጣ ፕሮጀክት መሆኑ ጥርጥር የለውም።ግድቡ ሲጠናቀቅ ወንዝ እየፈሰሰ ዝናብ የመጠበቅ ፖለቲካና የዓባይ ውሃ ጦርነት ኢ-ምክንያታዊነት አብሮ የሚጠናቀቅ እና ግብጾች ይዘውት የተነሱት የስግብግብነት ልጓም የሚገታ ይሆናል፡፡


እስካሁን በአፍሪካ ግዙፍ ግድቦች በራስ ሀብት ያለ ማንም የውጭ እርዳታ የተገነባ የለም። በፈርኦኖች ምድር የተገነባው የአስዋን ግድብ እንኳ በሶቪዬት ህብረት የገንዘብ ድጋፍ የተገነባ ነበር፡፡ግብጽ የሶቪዬት ህብረት ወዳጅነትን የሚያመለክት በአስዋን ግድብ አቅራቢያ 72 ሜትር ርዝመት ያለው ሀውልት አቁማለች፡፡ ታላቁ የህዳሴ ግድብ የ21ኛው ክፍለ ዘመን የአድዋ ድል ብስራት የፓን ኢትዮጵያኒዝም ርዕዮት ዓለም ግማድ ነው።


ምንም እንኳ የግድቡ መጠናቀቅ ቀደም ሲል እንደገለጽኩት ጥቅሙ የጋራ ቢሆንም የናይል ተፋሰስ አባል ሀገራት ከግብፅ ውጭ ማለቴ ነው በሄድ መለስ የፖለቲካ ጨዋታ ውስጥ የሚያልፉ ናቸው። የዚህ ጨዋታ ማጠናቀቂያ ፊሽካ ሊሆን የሚችለው ደግሞ ወንዛችንን ከእንጉርጉሮና ከማድመቂያ ሙዚቃ ወጥተን መጠቀምና ሁለንተናዊ የምጣኔ ሀብታችንን ማሳደግ ስንችል ነው።


ግብፅ ግን ይህን ዘመን ሁሉ የእጅ አዙር እና የውክልና ጦርነት ስታካሂድበት የቀጣናውን አባል ሀገራት በልዩ ልዩ መንገዶች አንዴ በጎሳ ሌላ ጊዜ በጥቅም እየደለለች ስታባላ ኑራለች። የህዳሴ ግድብ ይህን ሁሉ አደጋ መቀልበሻ ቦይ ነው። የአድዋ ጦርነት ዋና ግብ ጣሊያን የኢትዮጵያን የተፈጥሮ ሀብት መመዝበር እንደነበር ለማንም ግልጽ ነው። ጣሊያን ላሏት ፋብሪካዎቿ ጥሬ እቃ ፍለጋ እና በቀጣናው ያላትን ተስፋፊነት እና ተሰሚነት ማጎልበቻ አድርጋ ነበር የተነሳችው ።


የጣሊያን ተንኮል የገባቸው ኢትዮጵያዊያን ጀግኖች አርበኞቻችን የኢትዮጵያ የነፃነት ንስሮች ከሁሉም የሀገራችን ክፍል ነጋሪት ጎስመው ወደ አድዋ መትመም ጀመሩ። የጣሊያን የፊት አውራሪዎች በጥሬ እቃ ምዝበራ ፍጹም የታወሩ ግን ኢትዮጵያን እና ኢትዮጵያዊያን በሚገባ ያላወቁት ሰላቶዎች ስለነበሩ በአድዋ ተራሮች የኢትዮጵያን ጀግኖች ጎራዴ ፉጨትና የመልስ ምት መቋቋም ተስኗቸው በአድዋ ሰማይ ስር እንደ ጤፍ አዝመራ ተበተኑ፣ሄዱ፣ፈረጠጡ፣ሞቱ ተቀበሩ።ለዚህም ነው የታላቁ ህዳሴ ግድብ እና አድዋ የአንድ ሳንቲም ሁለት ገፅታዎች ናቸው የሚባለው፡፡


በህብር ወደ ብልጽግና !

ምላሽ ይስጡ