You are currently viewing አድዋ-የጥቁር ህዝቦች የነፃነት ተጋድሎ ቀንዲል /በሚራክል እውነቱ/

አድዋ-የጥቁር ህዝቦች የነፃነት ተጋድሎ ቀንዲል /በሚራክል እውነቱ/

  • Post comments:0 Comments

«እናንተ አንድ ልብ ከሆናችሁ በምቀኝነት እርስ በርሳችሁ ተዋግታችሁ ካላለቃችሁ በቀር ኢትዮጵያን አገራችንን ለሌላ ለባዕድ አትሰጧትም፤ ክፉም ነገር አገራችንን አያገኛትም። ነፋስ እንዳይገባባችሁ አገራችሁን በያላችሁበት በርትታችሁ ጠብቁ፤ ወንድሜ ወንድሜ እየተባባላችሁ ተደጋገፉ፤የኢትዮጵያን ጠላት ተጋግዛችሁ ተደንበር መልሱ።

የኢትዮጵያ ጠላት በአንዱ ወገን ትቶ ባንድ ወገን ቢሄድና ደንበር ቢገፋ፤ በኔ ወገን ታልመጣ ምን ቸገረኝ ብላችሁ ዝም አትበሉ፤ ያ ጠላት በመጣበት በኩል ኁላችሁም ሄዳችሁ አንድነት ተጋግዛችሁ ጠላታችሁን መልሱ እስከየ ቤታችሁ እስኪመጣ ዝም ብላችሁ አትቆዩ።» ዳግማዊ አፄ ምኒልክ ንጉሠ ነገስት ዘኢትዮጵያ ***********************************************************************በኢትዮጵያ አሸናፊነት የተጠናቀቀውና የጣልያን የቀኝ ግዛት ማስፋፋት ሴራ የተኮላሸበት የአድዋ ጦርነት የአንደኛው የኢትዮጵያና ጣሊያን ጦርነት ክፍል ነው። የአድዋ ድል የኢትዮጵያ ብሔራዊ ክብር ማኅተም፤ የጥቁር ህዝቦች የነፃነት ተጋድሎ ቀንዲል ነው፡፡ የመላው ዓለም ተፈጥሮአዊ ግብር እና ሰብአዊ ክብር የታደሠው፤ በእውነትና በፍትህ ህልውናና ምልዓት ላይ የተሰካ ትልቅ ጥርስ የተነቀለው በአድዋ የታላቅ ህዝቦች ታላቅ ድል ነው፡፡

የአድዋ ድል ኢትዮጵያዉያን ወራሪ ጠላትን ድል ያደረጉበት ብቻ አይደለም፤አድዋ ኢትዮጵያዉያን በአንድነትን ትብብርን ያሳዩበት ነዉ ማለት ይቻላል። ይህ ብቻ ሳይሆን ኢትዮጵያን አባት እና እናቶች ለዚህ ትዉልድ ያቆዩት ጠንካራ የማስተባበር፤ የመምራት፤ የመደማመጥ ችሎታቸዉም እንዳላቸዉ ያስመሰከሩበት ድል ነዉ።

አድዋ በቅኝ ግዛት ሥር ለነበሩ አፍሪካውያንና በሌሎች አህጉሮችም በጭቆና ውስጥ ለነበሩ ሕዝቦች የተስፋ ጭላንጭል ያሳየ ድል መሆኑን ዓለም ይረዳዋል፡፡ የዓድዋ ድልን ተምሳሌት በማድረግ በዓለም ላይ የነፃነት ትግሎች መፋፋማቸው የሚታወቅ ሐቅ ሆኖ ድሉ ለአገሪቱ ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካ እውነታ ያበረከተውን አስተዋጽኦ ታሪክ ሲዘክረው ይኖራል፡፡

ድሉ የአገር ፍቅር ስሜትና አንድነትን በማጠናከር፣ የዘመናዊነት መስፋፋት መነሻ በመሆንና አገሪቱ ከሌሎች አገሮች ጋር ሰፊ ዲፕሎማሲያዊ ትስስር እንዲኖራት ያስቻለ ሀገራዊ በዓላችን ነው፡፡ለፓን አፍሪካኒዝም ንቅናቄና አሁንም በአፍሪካ አገሮች መካከል ያለውን አህጉራዊ ትስስር በማጥበቅ ረገድ የአድዋ ድል መሠረት መጣሉ አፍርካዊያን ከልብ ይረዱታል፡፡

የአድዋ ድል ለኢትዮጵያዉያን ሁሉ ከጫፍ እስከጫፍ አምዳችን ነዉ፤ መሰረታችን ነዉ። አባቶቻችን ልዩነቶቻቸዉን ሁሉ ወደኋላ ጥለዉ ለሃገራቸዉ ከጫፍ ጫፍ ተነስተዉ፤ አንድ ቦታ ላይ አጥንታቸዉ ተፈጭቶ ደማቸዉ ፈሶ፤ የተቀላቀሉበት በአንድ መንፈስ ያሸነፉበት ታሪካዊ ድል ነዉ። ስለዚህ አድዋ ለሕዝባችን ሁሉ አምዳችን መቆምያችን መነሻችን ነዉ ብዬ አስባለሁ።

የአድዋ ድል ኢትዮጵያ ብቸኛ ነፃ የጥቁር ሃገር ሆና እንድትቆይ አባቶቻችን የከፈሉት ዋጋ በመሆኑ መላዉ የዓለም ጥቁር ሕዝብ እጅግ የሚኮራበት ድል ነዉ። ምክንያቱም አድዋ ታሪክን ቀይሯል። የአድዋ ድል አሜሪካን ጨምሮ በመላው ዓለም ለሚኖሩ ጥቁር ዜጎች እንደ ትልቅ የነጻነት ምልክት ሆኖ ይታያል።

አንድ ጥቁር ንጉስ ሕዝቡን አስተባብሮ በዓለም ላይ በታላቅ ስም በታላቅ ክብር ሃገሩን ነጻ አድርጎ መኖር የሚችልበት አዲስ ታሪክ የተፃፈበት ብሔራዊ ክብራችን ነው፡፡የዓድዋ ድል ሲዘከር ታሪኩን ከማውሳት ጎን ለጎን የዛሬይቱን ኢትዮጵያ ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ሁኔታም የመዳሰስ አዝማሚያ የታየባቸው የዓድዋ ድል መታሰቢያ ዝግጅቶች፣ በትናንትናና በዛሬ መካከል አንዳች ድልድይ ለመዘርጋት የታለመባቸው መሆናቸውን መረዳት ያስፈልጋል፡፡

በህብር ወደ ብልጽግና !

ምላሽ ይስጡ