• Post comments:0 Comments

በሚራክል እውነቱ

ከአገራዊው ለውጥ በኋላ በተገኘው ነጻነት እና ፍፁም ሀሳብን የመግለጽ ዴሞክራሲ ሰበብ በማድረግ ከሀገር ውስጥ የሚኖሩና ጥቅማቸው የተነካባቸው እፉኝቶችም ሆኑ ለውጡን በመከተል ወደ ሀገር ቤት የገቡ አንዳንድ የፖለቲካ ድርጅቶችና የመገናኛ ብዙኃን ተቋማት በሰላም፣ በፍቅርና ለዘመናት በአብሮነት በሚኖረው ህዝብ መሃል ግጭት ለመፍጠር ብሎም ሀገራዊ ለውጡን ለማጨናገፍ ጥረት ሲያደርጉ እንደነበር የአደባባይ ሚስጥር ነው፡፡

አብሮነታችንና በጋራ የመኖር ባህላችን ስር የሰደደ በመሆኑ ድብቅ የፖለቲካ ዓላማቸውን ለማሳካት ውዥንብር የሚፈጥሩ ግለሰቦችና ቡድኖች ፍላጎታቸው ህልም ሆኖ ይቀራል እንጂ ከቶውንም የአብሮነታችንን ገመድ ሊያላላ የሚችል አንዳች ነገር እንደማይኖር ህዝቡ ተረድቶታል፡፡

ከለውጡ ወዲህ ባሉ ሁለት ዓመታት ጥቅማቸው የተነካባቸውና ላለፉት ሀያ ሰባት ዓመታት ሀገሪቱን የመምራት ዕድል ቢያገኙም በህዝቡም ሆነ በሀገሪቱ ላይ ተጨባጭና መሰረታዊ ለውጥ ማምጣት የተሳናቸው አካላት በብሄር ብሄረሰቦችና ህዝቦች መካከል ጥርጣሬና መራራቅን በመፍጠር ለውጡን ለማደናቀፍ እና ኢትዮጵያዊ እሴቶቻችንን ለመሸርሸር እንቅልፍ አጥተው ሲሰሩ ይስተዋላል፡፡

በሀገሪቱ በሁሉም መስኮች የመጣውን ለውጥ ወደ ኋላ ለመመለስ የሚጥሩ ኃይሎች እየታገልን ወደ ብልጽግና የምናደርገውን ጉዞ እንቀጥላለን እንጂ በትናንሽ ፈተናዎች ተሸብበን እጅ አንሰጥም፡፡ይልቁንም የአብሮነትና የአንድነት እሴቶቻቸውን በማጠናከር በማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ መስኮች በንቃት በመሳተፍ ለጋራ ቤታችን እድገት ሚናችንን እንወጣለን እንጂ።

በአንዳችን ቤት የእሳት አደጋ፣ የጎርፍ አደጋ፣በተፈጥሮና ሰው ሰራሽ ምክንያት በሚፈጠር  መፈናቀል፣ ኃዘን፣ህመም፣ሞት ሲያጋጥመን እርስ በእርሳችን የምንረዳዳውና አብሮነታችንን የምናሳየው ወይም የምናዝነው ብሄር ወይም ኃይማኖት እየተጠየቅን ዓለመሆኑን መላው ዓለም የሚረዳው ሀቅ ነው፡፡ ለዚህ ማረጋገጫ ደግሞ እኛ ኢትዮጵያዊያን ለዘመናት ክፉውንም ሆነ ደጉን ጊዜ በጋራ ያሳለፍን ትሁት ህዝቦች መሆናችን በቂ ምስክር ነው፡፡

ሰላሜን ስጡኝ እያለ ሌት ተቀን የሚማፀን ህዝብ፣ የቀድሞው ወንድማማችነታችን ይበልጥብናል፣ አብሮነታችን ይሻለናል ተውን ሰላሜን ስጡኝ ፣ሰላማችንን አታደፍርሱብን የብዙሀኑ ድምፅ ነው፡፡

የሰላማችን መከበር የጀመርነውን የልማት ዕድገትና የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ለማረጋገጥ ብቻ አይደለም የሚረዳን፣ ይልቁንም የህዝቡን ሁለንተናዊ እንቅስቃሴ ያለገደብና ያለፍርሀት መንቀሳቀስም ያስችለዋል እንጂ፡፡ የሀገራችንን ሠላም ጠብቀን ለማስጠበቅ ደግሞ የግድ ከመንግስት የተመደብን  የፀጥታ ኃይል አባል መሆን የለብንም፡፡ በዜግነታችን ብቻ ከሁላችንም የሚጠበቅ ኃላፊነት ነው፡፡

ሰላም ለሀገራችን !

ጤና ለህዝባችን !

Leave a Reply