You are currently viewing በደቡብ ክልል በተፈጠሩ የጸጥታ ችግሮች እጃቸው ያለበት 711 አመራሮች ከሓላፊነት እንዲነሱ ተደርጓል – ክልሉ

በደቡብ ክልል በተፈጠሩ የጸጥታ ችግሮች እጃቸው ያለበት 711 አመራሮች ከሓላፊነት እንዲነሱ ተደርጓል – ክልሉ

  • Post comments:0 Comments

የደቡብ ክልል የመንግስት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ ሓላፊ ወ/ሮ ሰናይት ሰለሞን በክልሉ ላለፉት ሁለት ቀናት የተካሄደውን የመንግስትና የፓርቲ ተግባራት አፈጻጸም ግምገማ አስመልክቶ መግለጫ ሰጥተዋል፡፡የክልሉ ከፍተኛ አመራሮች እንዲሁም የዞን እና የልዩ ወረዳዎች ከፍተኛ የስራ ሓላፊዎች የተገኙበት የምክክር መድረኩ ያለፉትን 5 ወራት አፈጻጸም ገምግሟል፡፡

ወ/ሮ ሰናይት እንዳሉት መድረኩ አመራሩ በወቅታዊ ሀገራዊና ክልላዊ አጀንዳዎች ላይ በስፋት በመምከር የጋራ አቋም የያዘበት እና ቀጣይ ስራዎችን በብቃት ለመወጣት አቅጣጫ ያስቀመጠበት እንደነበር ገልፀዋል፡፡ሀገራዊ ለውጡን ተከትሎ ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ጉዳዮች ላይ የተመዘገቡ ውጤቶች ቢኖሩም ክልሉ በበርካታ ፈተናዎች ውስጥ ማለፉን ተናግረዋል፡፡

በክልሉ በጉራፈርዳ፤ በወላይታ በኮንሶ ዞን እና በዙሪያው ባሉ ልዩ ወረዳዎች ጽንፈኛው የህወሓት ጁንታ ሓይል ለግጭት አመቺ የሆኑ ቦታዎችን በመጠቀም እና የአደረጃጀት እና የወሰን ጥያቄዎችን መነሻ በማድረግ ህብረተሰቡ ያልተገባ ዋጋ እንዲከፍል ማድረጉን ወ/ሮ ሰናይት ተናግረዋል፡፡በብዝኃነቱ የሚታወቅና ለሌሎች አካባቢዎችም ተምሳሌት የሆነውን የደቡብ ክልል ጽንፈኛው ሓይል ለእኩይ አላማ ሲጠቀምበት እንደነበር በዝርዝር መገምገም እንደተቻለም ሓላፊዋ ገልጸዋል፡፡

ጽንፈኛው ቡድን ኢመደበኛ አደረጃጀቶችን በመጠቀም ሀብት በመመደብ ሲንቀሳቀስ መቆየቱንም አብራርተዋል፡፡በተፈጠረው ችግር በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ እጃቸው መኖሩ የተረጋገጠ 711 አመራሮች ከሓላፊነት እንዲነሱ ተደርጓል ብለዋል፡፡918 የሚሆኑት ከቦታቸው እንዲሸጋሸጉ ሲደረግ 1 ሺህ 966 ደግሞ በማስጠንቀቂያ መታለፋቸውን ገልጸዋል፡፡

ጽንፍ ይዘው የጸጥታ ችግሩን ሲመሩ እና ሲያስተባብሩ የነበሩ አመራሮች ደግሞ በሕግ ተጠያቂ እንዲሆኑ ተደርጓል ሲሉ ነው ሓላፊዋ በመግለጫቸው የጠቆሙት፡፡መጪው ሀገራዊ ምርጫ ነጻ፣ ፍትሓዊና ተአማኒነት ያለው እንዲሆን በሚያስችሉ የቅድመ ዝግጅት ስራዎች ላይ አመራሩ የጋራ አቋም እንደያዘም መናገራቸውን ከደቡብ ክልል መንግሥት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ ያገኘነው መረጃ አመልክቷል።

ምላሽ ይስጡ