ኢትዮጵያ ወደ ህዋ ያመጠቀቻት ETRSS-1 ሳተላይት ኦፊሴላዊ ርክክብ ተካሄደ።ኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ ከቻይናው ታዩዋን ከተማ የሳተላይት ማስወንጨፊያ ማዕከል ታህሳስ 10 ቀን 2012 ዓ.ም ወደ ህዋ ያመጠቀችው ETRSS-1 ሳተላይት ኦፊሴላዊ ርክክብ ተካሄደ።
ቀደም ብሎ በኢትዮጵያና በቻይና መካከል የዘርፉ መስሪያ ቤቶች በኩል ርክክቡን ለማከናወን ሲጠበቅ የነበረ ቢሆንም የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ መከሰት በፈጠረው የጉዞ መስተጓጎል ምክንያት ርክክቡ ሳይከናወን ቆይቷል።
በዚህም በሁለቱ መካከል ወገን በተደረሰ ስምምነት መሰረት በቻይና የኢ.ፌ.ዴ.ሪ. አምባሳደር ተሾመ ቶጋ እንዲረከቡ ተወስኖ በትናንትናው ዕለት በቤጂንግ ከተማ በቻይና የስፔስ ቴክኖሎጂ አካዳሚ (ካስት) ዋና መስሪያ ቤት በተካሄደ ስነ-ስርዓት ርክክቡ መፈጸሙን ኢዜአ ከቤጂንግ የኢትዮጵያ ኤምባሲ ያገኘው መረጃ ያሳያል።ኢትዮጵያ የመጀመሪዋ የመሬት መመልከቻ ‘ETRSS-1’ የተሰኘችውን ሳተላይት ወደ ህዋ ማምጠቋ ይታወሳል።