በሚራክል እውነቱ
ኢትዮጵያ በዲፕሎማሲው መስክ በዓለም መድረክ የተሻለ ቦታ እንዳላት ግልጽ ነው፡፡ ምንም እንኳን የአካባቢው ጂኦፖለቲካዊና የዓለም አቀፍ ተቀያያሪ ሁኔታዎች ተጽዕኖ ቢያሳድርባትም ሀገሪቱ በዲፕሎማሲው ዘርፍ በዓለም አቀፍ ደረጃ ያላት ተሰሚነት እያደገና እየጨመረ መምጣቱ መረዳት ይቻላል፡፡
በዓለም አቀፍ ደረጃ የኢኮኖሚ ቅርቃር ውስጥ ወድቀው በመነሳት መሰረታዊ እድገት ማስመዝገብ ከቻሉ አገሮች ውስጥ መገኘቷ በኢኮኖሚ ዲፕሎማሲው ዘርፍ እያደረገች ያለውን አበረታች እንቅስቃሴ ማሳያ ነው፡፡
ሀገራችን በሚቀያየር የዓለም የፖለቲካ ሁኔታ ውስጥ ብሔራዊ ጥቅሟን ቀጣይነት ባለው መልኩ ለማስጠበቅ የምትከተለው የኢኮኖሚ ዲፕሎማሲ ውጤት ያመጣ ስለመሆኑ ብዙዎችን ያስማማ ጉዳይ ነው፡፡
ኢትዮጵያ በዲፕሎማሲው መስክ ያላትን የካበተ ልምድ እና ብሄራዊ ጥቅሟን ባስጥበቀ መልኩ የዲፕሎማሲ ስራዋን አጠናክራ የምትቀጥል ይሆናል፡፡ የኢ.ፌ.ዲ.ሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ክቡር ዶ/ር አብይ አህመድ ወደ ስልጣን ከመጡ ባጭር ጊዜ ውስጥ በኢትዮጵያ የተመዘገበው ሁሉን አቀፍ ለውጥ በዓለም ዓቀፍ ደረጃ እውቅና እንድናገኝ ያደረገና ያለንን ስትራቴጂያዊ ግንኙነት ያጠነከረ ነበር፡፡
በኢትዮጵያ እና በኤርትራ መካከል የተደረሰው የሰላም ስምምነት ከሁለቱ አገሮች ባሻገር በአፍሪካ ቀንድ ብሎም በአፍሪካ ባጠቃለይ የኢኮኖሚ ውህደት እንቅሰቃሴ ላይ አዎንታዊ ተጽዕኖ ያሳረፈ መሆኑ ብቻ ሳይሆን ሀገራዊና ቀጠናዊ ሰላም በኢትዮጵያ መንግስት የሚሰጠውን ከፍ ያለ ስፍራ ያሳየንበትም አጋጣሚ ነበር ማለት ይቻላል፡፡
በቅርቡ ዘራፊውና ጁንታው የህወኃት ቡድን በሰሜን ዕዝ ላይ ያደረሰውን ጥቃት አስመልክቶ መንግስት እየወሰደ ስላለው ሕግን የማስከበርና ህልውና ዘመቻ ዓላማ በተመለከተ በቀጠናውና ከቀጠናው ውጭ ላሉ ሌሎች የአውሮፓ ሀገራት ማብራሪያ በመስጠት ዲፕሎማሲያዊ ስራዎች በስፋት እየተሰጡ ይገኛሉ፡፡
ይህ አይነቱ የዲፕሎማሲ ስራ በኢትዮጵያ ስለተፈጠረው ወቅታዊ ሁኔታ ማብራሪያ መስጠት ብቻ ሳይሆን ዓላማው ከዚህም በዘለለ ከሌሎች ሀገራት ጋር ያለንን ወዳጅነት የምናጠናክርበትና ለሉዓላዊነታችን የምንሰጠውን ከፍ ያለ ቦታ ለማሳየትም ጭምር ነው፡፡ በክቡር አቶ ደመቀ መኮንን እና በክቡር አቶ ገዱ አንዳርጋቸው በሁለት አቅጣጫ የሚመራው የዲፕሎማሲ ስራ ውጤታማ እንደሆነ ግልጽ ነው፡፡
በምክትል ጠ/ሚኒስትርና በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ክቡር አቶ ደመቀ መኮንን እስካሁን በአውሮፓ እየተደረገ ያለው ኢትዮጵያ እየወሰደችው ያለው ህግን የማስከበር ዘመቻ ማብራሪያ ሀገራት በአግባቡ መገንዘባቸውንና የውስጥ ጉዳይ መሆኑንና የማንም ጣልቃ ገብነት እንደማያስፈልግ በአንደበታቸው ሲናገሩ ተደምጠዋል፡፡
የየሀገራት መሪዎች በአንድ ቃል የሚገልጹት ግን በተቻለ መጠን በሚደረገው ህግን የማስከበር ዘመቻ ንጹሃን ዜጎች ተጎጂ እንዳይሆኑ ጥንቃቄ መወሰድ አለበት የሚል ነው፡፡ይህ ደግሞ ሰራዊታችን እስካሁን ባለው ዘመቻ የሞተም ሆነ የተጎዳ ሰው አለመኖሩ ምን ያህል ዘመቻው በጥንቃቄ እየተፈጸመ እንዳለ ማሳያ ነው፡፡
በቅርቡ እየተካሄደ ያለውና ኢትዮጵያ ያለችበትን ወቅታዊ ሁኔታ የማስረዳት ዘመቻ በኢትዮጵያ ሰላም፣ ዲሞክራሲና ተጨባጭ እድገት ለማምጣት በሚደረገው ርብርብ እንዲሁም ለቀጠናዊ ውህደት የሚጠበቅብንን ሚና በአግባቡ ለመወጣት የሚያስችል አቅም ከመገንባት በተጨማሪ ስትራቴጂያዊ አጋሮችን ማፍራትና ለአገሪቱ ሁሉን አቀፍ እድገት ምቹ መደላድል መፍጠር እንደሆነ መረዳት አያዳግትም፡፡ ይህ ደግሞ አሁን ላለንበት ሁኔታ በእጅጉ አስፈላጊ የዲፕሎማሲ ስራ ነው፡፡ ይህንን ተልዕኮ በማሳለጥ በኩል ደግሞ አገራችን በተለያዩ የዓለም አገራት ያሉ ኤምባሲዎችና ቆንስላ ጽህፈት ቤቶች ከፍተኛ የሆነ የፖለቲካና የኢኮኖሚ የዲፕሎማሲ ስራ በመስራት ላይ ይገኛሉ፡፡
ሀገራችን የምትገኝበትን ወቅታዊ ሁኔታ ለሀገራት የማስረዳት ፖለቲካዊ የዲፕሎማሲ ስራ እየቀጠለ ጎን ለጎን በአምባገነኑ እና ጁንታው የህወኃት ቡድን ላይ እየተወሰደ ያለው ህግን የማስከበርና የህልውና ዘመቻ አጠናክሮ በማስቀጠል ወንጀለኞች በአደባባይ ለፍርድ እንዲቀርቡ የማድረጉ ስራ ይቀጥላል፡፡ ዓለም ከእኛ ጋር ነው !
ሰላም ለሀገራችን !ጤና ለህዝባችን !