ከኢትዮጵያዊነት ይልቅ በፓርቲ አስተሳሰብ በታጠሩ ከሃዲ ጀኔራሎች የሚመራው የህወሓት ጁንታ ከፍተኛ ሽንፈት እየተከናነበ መሆኑን የልዩ ዘመቻ ኮማንዶ አባላት ገለጹ።የህወሓት ጁንታ በግዳጅ ሲያዋጋቸው የነበሩ በርካታ የልዩ ሃይል አባላት ለአገር መከላከያ ሠራዊት እጃቸውን እየሰጡ ይገኛሉ።የልዩ ዘመቻ ኮማንዶ ዋና አዛዥ ኮሎኔል ከማል አቢሱ ህወሃት የኢትዮጵያ ዘብ የሆነውን የመከላከያ ሠራዊት በዘርና በአስተሳሰብ መርዞ ለመከፋፈል ሲጥር እንደነበር ገልጸዋል።
ቡድኑ ይህም አልበቃ ብሎት ከኪሱ ቀንሶ ለትግራይ ሕዝብ የጤና ተቋምና ትምህርት ቤቶችን በመስራት ወገንተኝነቱን በተግባር ባሳየው የአገር መከላከያ ሠራዊት ላይ የክህደት ጥቃት መፈጸሙን አስታውሰዋል።
በመሆኑም መከላከያ ሠራዊቱ ይህን ቡድን በገባበት ገብቶ በመደምሰስ አንፀባራቂ ድል እያስመዘገበ መሆኑን የገለጹት ኮሎኔል ከማል፤ “ቡድኑ ፈልጎ በከፈተው ጦርነት ድባቅ እየተመታ ነው” ብለዋል።የህወሃት ጁንታ ከሰራዊቱ የዘረፋቸውን መሳሪያዎች ታጥቆና ኢትዮጵያዊነትን ከውስጣቸው ሰርዘው በፓርቲ በታጠሩ ከሃዲ ጀኔራሎች እየተመራ ከንቱ የጥፋት ሙከራ በማድረጉ በወገን ሠራዊት ባለበት መደምሰሱንና ገሚሱ ወደኋላ መፈርጠጡን ተናግረዋል።
ሌተናል ኮሎኔል ሳዲቅ አህመድ በበኩላቸው “ጁንታው በእብሪት በጀመረው ጦርነት በሁሉም አቅጣጫ ሽንፈትን አስተናግዷል” ብለዋል።“በራያ ግንባር አንድ ዓመት ያዋጋኛል፤ የመከላከያ ሠራዊቱንም እደመስስበታለሁ ብሎ በገነባው ሁለት ዙር ምሽግ ሶስት ቀን ሳይዋጋ ተደምስሷል” ነው ያሉት።የቡድኑ ታጣቂ ሃይል የእብሪት ፉከራ ባዶ ቀርቶ መሳሪያውን እያንጠባጠበ መሸሹን ገልጸዋል።
“የጁንታውን ቡድን በሚገባ እናውቀዋለን” ያሉት ሌተናል ኮሎኔል ሳዲቅ፤ ቡድኑ በሀሰት ፕሮፓጋንዳ ሕዝብ ከማደናገር ባለፈ አቅሙ በከፍተኛ ደረጃ መዳከሙን ተናግረዋል።“ሴት የመከላከያ ሠራዊት አባላት ከወንዶች ጋር በመሳተፍ በእልህና በወኔ የጁንታውን ምሽግ እያፈራረሱ ይገኛሉ” ያሉት ደግሞ የኮማንዶ አባል የሆኑት ወታደር ዓለምፀሀይ ታረቀኝ ናቸው።“ሕግ የማስከበር ዘመቻው ዳር እስከሚደረስ ሠራዊቱ በቁርጠኝነት ወደፊት ይቀጥላል” ብለዋል።