You are currently viewing የዘመኑ የትሮይ ፈረሶች

የዘመኑ የትሮይ ፈረሶች

  • Post comments:0 Comments

                                          (በአሮን ተወልደ)

ማታለል እና ማጭበርበር በእኛ ባህልና ወግ እጅጉን የሚወገዝና ማህበረሰባችንም አብዝቶ የሚጸየፈው አስነዋሪ ተግባር ነው፡፡ የማታለል ግቡ ሌብነት እና ቀጣፊነት በመሆኑ ከእኛ ወግ እና ባህል እጅጉን የተቃረነ፤ ከማህበረሰቡ የሚነጥል እኩይ ባህሪ ነው፡፡ ይህ የቅጥፈት መንገድ በእሾህ ላይ እንደመረማመድ፤ ሰውነትንም እንደመካድ ነው፡፡ ቅጥፈት ለእውነት የቆመን ሰው ጭምር አታልሎ መቀመቅ የሚከት የትሮይ ፈረስ ነው፡፡ የትሮይ ፈረሶች እምነትን ለክህደት፤ አብሮነትን ለጥቃት፤ አንድነትን ለብተና የሚጠቀሙ በጤናማ አስተሳሰብ እና አረዳድ ውስጥ ተሰንቅረው ጥፋት እና ውድመትን የሚደግሱ እኩያውያንን የሚገልጽ ነው፡፡ ለዚያም ነው ትሮያውያኑ በደጃፋቸው ያገኙትን የተቀረጸ የፈረስ ምስል ከአማልክት የተላከ ስጦታ ወይም ከግሪኮች የተበረከተላቸው የእጅ መንሻ እንጂ ነገሩ ሊያጠፋቸው የተላከ አማላይ ሰንኮፍ ስለመሆኑ ያልተጠራጠሩት፡፡ በተመሳሳይ በዘመናችንም የትሮይ ፈረሶች እስስትነትን ብዙዎቹ ቀድመው ቢረዱ ኮምፕተሮች እና የግለሰቦች መረጃ የሳይበር ቀበኛ ሲሳይ ሆነው እንዳልነበር ባልሆኑ ነበር፡፡ የትሮይ ፈረሶች የራሳቸው ህልውና የሌላቸው፤ የጌቶቻቸው አገልጋዮች፤ የአጉራሻቸው ካዳሚ ናቸው፡፡

እናም የትሮይ ፈረሶችን የጥፋት ማልዕክተኛነት እና ባህሪን መረደት ሊደርስ የሚችለውን ጉዳት እና ውድመትን ለመቀነስ ያስችላል፡፡ ሆኖም ግን ባህሪያቸው እጅጉን ከጤናማ ነገሮች ጋር ስለሚመሳሰል የትሮይ ፈረሶችን ማጥፋት አዳጋች ሊሆን ይችላል፡፡ ለዚያም ነው የትሮይ ፈረስ የጥፋት አድማስ በጥንታዊቷ ግሪክ ወይም በኮምፕዩተር ላይ ብቻ ያልተገታው፡፡ በተለይም ሁለት እግር ያላቸው ውሸት ጋላቢ የትሮይ ፈረሶች የሰው ልጆች የህልውና ስጋት ስለመሆናቸው በርካታ ማሳያዎችን መጥቀስ ይቻላል፡፡ በዚህ ጎራ ያሉትን የትሮይ ፈረሶችን እጅግ አደገኛ የሚያደርጋቸው ደግሞ ለህሊና መገዛት የሚለውን ቀረጣጥፈው የበሉ እና ቅጥፈትን ግብራቸው ያደረጉና ከሰብዓዊነት ጋር የተቃረኑ ፍጡራን መሆናቸው ነው፡፡ ከሁሉም በላይ ግን ሀገርን ማፍረስ ‘ክብራቸው’ ያደረጉ ከሰውነት ልክ የወረዱ መሆናቸው ነው፡፡

ከሰሞኑ ካሃዲውን የህወሓት ቡድን ለሕግ ለማቅረብ ብሎም ሕግ እና ስርዓትን ለማስከበር መንግስት እያደረገ ያለውን እንቅሰቃሴ ለማደናቀፍ  በለስ ከቀናቸውም ለመቀልበስ ቡድኑ በራሱ አምሳል ቀረጾ ያሰመራቸው የትሮይ ፈረሶች ባገኙት አጋጣሚ ከሚችሉት በላይ ሲጋጋጡ ተመልክተናል፡፡ ቀጣፊዎቹ የጁንታው ፈረሶች ህዝብን እና አለም አቀፉን ማህበረሰብ ለማታለል እና ለማወናበድ ያዋጣል ያሉትን የውሸት ዓይነቶችን በጅምላ እና በችርቻሮ ለማከፋፈል ኳትነዋል፡፡ መሬት ላይ ያለውን እውነታ በተቃራኒው ለማቅረብ ያልፈነቀሉት ድንጋይ ያላንኳኩት በር የለም፡፡  

በክልሉ ጁንታው በመሰረተ ልማቶች ላይ ባደረሰው ጥፋት የኢንተርኔት አገልግሎት በመቋረጡ አብዛኞቹን እና መቀሌ የመሸጉትን የቡድኑ ቅልብ ፈረሶችን ከጨወታው ሜዳ ቢያሥወጣም፤ ጥቂቶቹ ህወሓት ሰራሽ የትሮይ ፈረሶች ግን አሁንም ባገኙት አጋጣሚ ጁንታውን ለማዳን መፍጨርጨራቸውን ቀጥለዋል፡፡ እነዚህ ጁንታው የሚጋልባቸው ጭራ አልባ እና ራጃጅም ምላስ ያላቸው ትሮዮች ውስጣቸው ያለውን መርዝ በመደበኛው ሚዲያ እና በማህበራዊ ሚዲያ አማካኝነት የቻሉትን ያክል ለመንዛት ሞክረዋል፤ እየሞከሩም ነው፡፡ ጥቂቶች የትግራይ ህዝብ ንብረት በሆነው እና ለጊዜው የጁንታው መጠቀሚያ በሆነው የትግራይ ቴሌቭዥን የውሸት ጋጋት ሲያሽጎደጉዱ ሰንብተዋል፡፡ በጀግናው የሀገር መካላከያ ሰራዊት ግስጋሴ የካሃዲው ቡድን ትሮዮች ከመርበትበታቸው የተነሳ በቀመሩት ውሸት ላይ እንኳን ለመግባባት እየተቸገሩ፤ አንዱ ያለውን ሌላው ሲያፈርሰው ተመልክተናል፡፡ አንደኛው የጁንታው አባል ሰሜን እዙ በይሁንታ ከነሱ ጋር አንዳበረ ለማሳመን ሲጋጋጥ፤ ሌላኛው ደግሞ ጁንታው በራሱ ቅዠት ተደናብሮ እዙን እንደተተናኮለ በይፋ ለፍልፏል፡፡ ይህ የትሮይ ፈረሶች ባህሪይ ነው፤ ባገኙት አጋጣሚ መርዝ መርጨት  እና ከተሳካ  በመመረዝ፤ አብዛኛውን ወይም ሙሉ በሙሉ ማውደም፤ አሊያም በማደናገር ቀጣዩን ለውሸት መቀመሚያ የሚሆን ጊዜ መግዣ ማድረግ፡፡

የእስትንፋሳቸው ገመድ ከካሃዲው ቡድን ጋር እጅጉን የተቆራኘ የህወሃታዉያኑ ትሮዮች የሚረጩት መርዝ ሀገርን እንዳይመርዝ ሰንኮፉን ለመንቀል ህዝቡ እየተረባረበ በሚገኝበት በዚህ ወቅት በተለመደ ቅጥፈታቸው የበለጠ ጥፋት ለማድረስ ሲራወጡ ይታያል፡፡ እናም ያልበረረ ጀት ‶ሲደመስሱ‶ በቅዥት መመላለሱን ቀጥለዋል- ቅጥፈት ግብራቸው፤ ማምታት ስልታቸው ነው፡፡ ምን ይታወቃል የእነሱ ቅጥፈት እኮ ምናልባትም በለስ ቀንቷቸው በሕግ ጥላ ስር ቢሆኑ እንኳን ‶ደምስሰናል፤ ማርከናል‶  ይሉ ይሆናል….ምክያቱም ቅጥፈት የካሃዲው ቡድን ትሮያውያን ዓይነተኛ ባህርይ ነው፡፡

ሀፍረት የማይሰማቸው የካሃዲው ቡድን አገልጋዮች በለስ ከቀናቸው የአለም ቀፉን ማህበረሰብን በማጭበርበር ቡድኑ አፈር ልሶ እንዲነሳ ቀን ከሌሊት የሚጋልቡ ናቸው፡፡ ለዚህ ደግሞ የማህበራዊ ሚዲያውን አውድ እንደመልካም አጋጣሚ በመጠቀም ቅጥፈታቸውን አጧጡፈዋል፡፡ ከሀገር እስከ አለም አቀፍ ማህበረሰብ እና ሚዲያ ዒላማ አድርገው እየተንቀሳቀሱ ይገኛሉ፡፡ ሀገር ሆነ ህዝብ፤ ተቋም ሆነ ግለሰብን ከማጥፋት እና መጠቀሚያ ከማድረግ ወደ ኋላ እንደማይሉ አሳይተዋል፡፡ እናም አስመሳዮቹ እና አጭባርባሪዎቹ የከሃዲው ቡድን ትሮያውያን ለማንም እደማይመለሱ መገንዘብ ያስፈልጋል፡፡ መገንዘብ ብቻ አይደለም ሁሉም በያለበት የነዚህን እኩይ ተግባር ለአለም አቀፉ ማህበረሰብ ማጋለጥ እና ማስረዳት ይጠበቅበታል፡፡

ምላሽ ይስጡ