የሰራዊታችን በተግባር የተመዘነ ህዝባዊነት…

የሰራዊታችን በተግባር የተመዘነ ህዝባዊነት…

  • Post comments:0 Comments

በሚራክል እውነቱ

ሰራዊታችን በየተሰማራባቸው የሰላም ማስከበር ግዳጆች ላይ የፈጸማቸውን ገድሎች  በሙሉ አንስቶ መጨረስ  አይቻልም፡፡ ሰራዊታችን ችግር የማይበግረው፤ ፈተና ከኢትዮጵያዊነቱ ፈቀቅ የማያደርገው ከህዝብ ወጥቶ ለህዝብ የሚኖር ዕንቁ የሀገር ሀብት ነው፡፡

ጠላት ሀገርን ሊወር ከሩቅ ሲመጣ ከህዝብ ቀድሞ ግንባሩን ለጥይት የሚሰጥ፣ ለሀገር ኖሮ፣ ለህይወቱ ሳይሳሳ ግንባር ተሰልፎ፣ ለሀገር ተዋግቶ፣ ለሀገር ቆስሎ ለሀገር የሚሞት የኢትዮጵያዊነት መሰረት ነው፡፡ የአገር መከላከያ ሰራዊት፡፡

በሰላሙም ጊዜ ህዝብን መስሎ የሚኖር፣ ህዝብ ሲቸገር ቆሞ ማየት የማይችል እንስፍስፍ ልብ ያለው፣ ዜጎች በደም እጦት ምክንያት ህይወታቸው እንዳያልፍ ዳር ድንበሩን እየጠበቀ ደሙን ሳይሰስት የሚሰጥ የህዝባዊነት ምልክት ነው፡፡ ሰራዊታችን በተፈጥሮና በሰው ሰራሽ ምክንያት አገልግሎት መስጠት ያልቻሉ ድልድዮችንና መንገዶችን ጉልበቱን፣ ገንዘቡንና ዕውቀቱን አጣምሮ ለህዝብ ጥቅም የሚያውል ከራሱ በላይ ለህዝብ የሚኖር የመልካም ስብዕና ባለቤት ነው፡፡   

ጁንታው የህወኃት ቡድን “እኔ ከሞትኩ ሰርዶ አይብቀል” በሚል እሳቤ በሰራዊታችን የሚቃጣበትን ጥቃት መቋቋም ሲሳነው በህዝብ ሀብት የተሰሩ ድልድዮችን፣ መንገዶችንና አየር መንገዶችን ከጥቅም ውጭ ሲያደርግ ተመልክተናል፡፡ ይሁን እንጂ ሁለገብ የሆነው ሰራዊታችን ከዚህ ቀደም በተለያዩ የግዳጅ ግንባሮች እንደሚያደርገው ሁሉ ጠላት የሆነውን ህወኃት እየተዋጋ ጎን ለጎን በጥፋት ቡድን ጥቃት የተፈጸመባቸው መሰረተ ልማቶችን እየጠገነ ለአገልግሎት እንዲበቁ ማድረግ ችሏል፡፡

ሰራዊታችን አርሶ አደር ነው፤ ከአርሶ አደሩ ጋር አርሞ፣ አጭዶ ጎተራ የሚያስገባ ገበሬ፤ አርብቶ አደርም ነው፡፡ መሐንዲስም ነው፡፡ መልካዓ ምድራዊ አቀማመጣቸው በእጅጉ ፈታኝ የሆኑ አካባቢዎችን ሀላፊነት ወስዶ ጋራ ሸንተረሩና ሸለቆው ሳይበግረው መንገድና ድልድይ ስርቶ ማስረከብ የሚችል የታታሪነት ተምሳሌት፡፡

ሰራዊታችን በገጠራማ አካባቢዎች የሚኖሩና በቂ የህክምና አገልግሎት ማግኘት ላልቻሉ ነዋሪዎች ከተማ ድረስ ሄደው ህክምና እንዲያገኙ በርካታ አምፑላንሶችን ገዝቶ ለወለደው ህዝብ እንካችሁ የሚል ከህዝብ ወጥቶ ለህዝብ እየኖረ ያለ ርሁሩህ ሰራዊት ነው፡፡

ሰራዊታችን የሰላም ሰባኪም ነው፡፡  ስለ ጦርነት አስከፊነትና ስለሚያደርሰው እልቂት፣ ስለ ሰላም ሀያልነት ሌት ተቀን ቆሞ ህዝብን የሚሰብክ፣ የሚያስተምርና የሚመክር ድንቅ ፍጡር፡፡ ሰራዊታችን ሁሉንም መሆን የቻለና የሚችል የብሔር ብሔረሰቦች ስብስብ ነው፡፡ ለዛም ነው ሰራዊታችን ዛሬም ህዝባዊነቱን ጠብቆ የንጹሃንን እልቂት በመቀነስ አጥፊ ቡድኑን ነጥሎ ለማስወገድ ራሱን መስዋዕት እያደረገ በጥበብ እየተንቀሳቀሰ ያለው፡፡

ሰራዊታችን በዘራፊውና አምባገነኑ ቡድን ላይ እየተወሰደ ያለውን ህግን የማስከበርና የህልውና ዘመቻ ላይ እጅግ በረቀቀ መንገድ፣ ብስለት በተሞላበት አካሄድ በተመረጠና በተጠና ሁኔታ ጁንታውንና ጄሌዎቻቸውን ለይቶ በማጥቃት ከምንም በላይ ወልዶ ባሳደገው ህዝብ ላይ ምንም አይነት አላስፈላጊ ጉዳት እንዳይደርስበት በማሰብ ተልዕኮውን በጥንቃቄ እየፈጸመ ይገኛል፡፡ ዛሬም ነገም ወደፊትም የድልና የኢትዮጵያዊነት ምልክት ሆኖ ይቀጥላል፡፡

ድል ለሰራዊታችን !!

Leave a Reply