የማይነጥፈው የህወሓት ጁንታ ቅጥፈት

የማይነጥፈው የህወሓት ጁንታ ቅጥፈት

  • Post comments:0 Comments

በዜማ ያሬድ

የህወሓት ቅጥፈት የሚጀምረው ገና ከስሪቱ ቢሆንም ከለውጡ በኋላ ግን በጥላቻና በትዕቢት ተለውሶ ይበልጥ እየተገለጠ መጥቷል፡፡ በአገራችን በህዝብ ዘንድ የተቀጣጠለው የለውጥ ፍላጎት መሬት እየነካና ህዝቡ የለውጡ ጉልበት እየሆነ መምጣት ከጀመረበት ጊዜ ጀምሮ በእኔ ብቻ አባዜ አቅሉን የሳተው የህወሓት ጁንታ ቡድን የማዕከላዊ መንግስቱን ጠላት አድርጎ በመፈረጅ፤ አልፎ ተርፎም በየአካባቢው እኩይ ተግባራትን በመፈጸም መንግስት ጣት እንዲቀሰርበትና እንዲዳከም ለማድረግ ያልፈነቀለው ድንጋይ አልነበረም፡፡

ቡድኑ የለውጡ መጀመሪያ አካባቢ ደጋፊ በመሆንና ሂደቱን ጭምር የጋራ አድርጎ በመንቀሳቀስ ከስህተቱ ተምሮ ህዝብ ለመካስ የተዘጋጀ መስሎ ቢቀርብም አዲስ አበባ አንድ ቃል፤ ወደ ምሽጉ መቀሌ ሲሄድ ደግሞ ሌላ ቃለ በመናገር እምነት የማይጣልበት ከሃዲ ቡድን መሆኑን በራሱ መንገድ ለህዝብ እያረጋገጠ መጥቷል፡፡

የዚህ ቡድን ቅጥፈት ከመቼውም ጊዜ በላቀና ህዝብን ጥፋት ውስጥ በሚከት ሁኔታ ጎልብቶ እታገልለታለሁ የሚለውን ህዝብ ጭምር በእሳት ወደመማገድ ተሸጋግሯል፡፡ የህወሓት ጁንታ ቡድን፡፡ሁላችሁም እንደምታስታውሱት የለውጡ ጅማሮ አካባቢ የህወሓት ጁንታ ቡድን አዲስ አበባ ቁጭ ብለው የመከሩበትንና የተስማሙበትን ሃሳብ መቀሌ ሲሄዱ ሲያፈርሱት አስተውለናል፡፡

አንድ የሚመስሉ ግን አንድ ያልሆኑ፤ ጥቅም ብቻ ያቆራኛቸው የጁንታው ስብስብ እርስ በእርስ ጭምር የተውረገረገ ሃሳብ በመሰንዘር ህዝብ ሲያደናግሩ ማየት የተለመደ ሆኗል፡፡ በአማርኛ አንድ መግለጫ በትግርኛ ሌላ መግለጫ እየሰጡ ህዝቡን ሲያወናብዱት፤ ግራ ሲያጋቡትና በሃሰት ፕሮፓጋንዳ ሲመርዙት ቆይተዋል፡፡ ይህ አዲስ አበባ እየማለ እየተገዘተ መቀሌ ሲሄድ ክህደት የሚፈጽመው ቡድን ነው እንግዲህ ዛሬም በለመደው መንገድ እየዘላበደ ንጹሃንን ግፋ በለው ሲል የሚታየው፡፡

የህወሓት ጁንታ ቡድን በሰሜን እዝ ሰራዊት ላይ የፈጸመው ክህደትን ተከትሎ በአንድ እራስ ሁለት ምላስ እንዲሉ በቴሌቭዥን መስኮት የራሱን መግለጫ እራሱ እያፈረሰው ቅጥፈቱን ለአደባባይ አውሎታል፡፡ ከመነሻውም ከጀርባው ለመውጋት ያልሳሳለትን ሰራዊት ከእኔ ጋር ነው፤ ሙሉ የሰራዊቱ ድጋፍ አለኝ ባለ ማግሰት በአፈ ቀላጤው አማካኝነት ወጥቶ ለሰሚ እንኳን በሚከብድ መልኩ ለአገርና ህዝብ ክብርና ሰላም የቆመው ሰራዊት ላይ ጥቃት መፈጸሙን በገሃድ አመነ፡፡

ይህ ከሃዲ ቡድን በጀግናው መከላከያ ሰራዊት የተደመሰሱበትና በውንብድና ዘርፎ ለጥፋት ያዘጋጃቸው የጦር መሳሪያዎችን ካልሆነ በቀር ለዓመታት አምኖት የኖረውን ሰራዊት ከጀርባው ከወጋ በኋላ በምን ሞራሉ ከጎኔ ነው ሊል ይችላል፡፡ በእርግጥም ይህ ነው ሌላው የህወሓት የቅጥፈት ጥግ ተጨባጭ ማሳያ ነው፡፡ ሌላው የዚህ ጁንታ ቅጥፈት እያሸነፍን ነው፤ እየማረክን ነው እያለ ህዝቡን የሚያታልልበት ሁኔታ ነው፡፡

ሰራዊቱ በድል ታጅቦ ወደፊት እየገሰገሰ መሆኑ እውነት ሆኖ ሳለ ይህ ህዝብን እያታለለ የሚኖረው ጁንታ ዛሬም የጦር ቅስቀሳ በማድረግ ውሃ ያላጠጣውን ህዝብ ለመስዋዕትነት አዘጋጅቶታል፡፡ ይህ ጁንታ በአንድ በኩል ይህን ክፈለጦር ማርኬ፤ ደምስሼ የሚል ባዶ የጀብደኝነት ፕሮፓጋንዳ በመንዛት ሌላ ተጨማሪ ጥፋትና ክህደት በትግራይ ህዝብ ላይ እየፈጸመ ይገኛል፡፡

በጥቅሉ የህወሓት ጁንታ ቡድን በአንድ እራስ ሁለት ምላስ ነው፡፡ ተሸንፎ አለሁ የሚል፤ እየሞተ አልተቀበርኩም ብሎ የሚለፍፍ፤ ህዝብ ከጎኑ ሳይሆን ከጎኔ ነው እያለ ራሱን የሚያታልል ፍጹም ፀረ ህዝብ የሆነ እኩይ ቡድን ነው፡፡ ይህ ቡድን ግብዓተ መሬቱ ሊፈጸም ዳር ደርሷል፡፡ አሁን ጉዳዩ ንጹሃን መስዋዕት እንዳይሆኑ የሚገባውን ጥንቃቄ ማድረግ ነው፡፡ ለዚህ ደግሞ የህዝብ ልጅ የሆነው ሰራዊት ራሱን መስዋዕት አድርጎ ኦፕሬሽኑን ጁንታው ባሰበው መልኩ ሳይሆን በተለየ ጥበብ በድል ታጅቦ እየገሰገሰ ይገኛል፡፡

ድል ለሰራዊታችን፡፡ ድል ለኢትዮጵያ ህዝብ፡፡

Leave a Reply