የትግራይ ህዝብ ከደረሰበት የአምባገነኑ ጭቆና ነጻ ይወጣል…

የትግራይ ህዝብ ከደረሰበት የአምባገነኑ ጭቆና ነጻ ይወጣል…

  • Post comments:0 Comments

በሚራክል እውነቱ

ዘራፊውና ጽንፈኛው የህወኃት ቡድን ዛሬም ድረስ ምሽግ ውስጥ ሆኖ እጅ አልሰጥም አሻፈረኝ እንዳለ ነው፡፡ ተወደደም ተጠላም የፌደራል መንግስት ህግ የማስከበርና የህልውና ዘመቻውን አጠናክሮ በማስቀጠል እምቢተኛውን የህወኃት ቡድን ለህግ ማቅረቡ አይቀሬ ነው፡፡

አምባገነኑ የህወኃት ቡድን ዛሬም እንደትናንቱ ከህዝብና ከሀገር ይልቅ የራስን ምቾት በማስቀደም ዕድሜያቸው ለውትድርና ያልደረሱ አያሌ ወጣቶችን አስከፊ ለሆነው ጦርነት መጠቀሚያ እያደረጋቸው ይገኛል፡፡ ይህ ግራ የተጋባው ከሃዲው ቡድን መሰረታዊ ዓላማው ሀገርን ማፈራረስ እንደሆነ ለማንም የተደበቀ አይደለም፡፡

ከተቋማቱ ተልዕኮ ውጭ በሆነ መንገድ በማስፈራራት አልያም ሀይል በመጠቀም መቀሌ የሚገኙ ቤተ እምነቶችን እንደ ምሽግ እየተጠቀመባቸው ይገኛል፡፡ ቤተ እምነቶችን ለመሳሪያ ክምችት እና ለፕሮፖጋንዳ ስራ መጠቀም ጀምሯል፡፡ ይህ አይነቱ አካሄዱ በዓለም ላይ ታይቶም ሆነ ተሰምቶ አይታወቅም፡፡

የትኛውንም መስዋዕትነት ከፍሎም ቢሆን ሰራዊቱ እያደረገ ያለውን የትግራይን ህዝብ ከአምባገነኑና ከዘራፊው የህወኃት ቡድን ነጻ የማውጣት ተጋድሎ ዛሬም እንደትናንቱ በድል ማጠናቀቁ አይቀሬ ነው፡፡ ምክንያቱም የትግራይ ህዝብ ብቻ ሳይሆን መላው ኢትዮጵያዊያን ሰላም ናፍቋቸዋል፤ የህግ የበላይነት በተግባር ሲረጋገጥ ማየት ይፈልጋሉና፡፡

“መብሰሉ ላይቀር ማጋዶ ይጨርሳል” ነውና ነገሩ ጁንታው የህወኃት ቡድን የቀረበለትን በሰላም እጅ የመስጠት ጥሪ አሁንም የተቀበለው አይመስልም፡፡ ይህ ደግሞ በሁሉም መልኩ አላስፈላጊ መስዋዕትነት ማስከፈሉ አይቀርም፡፡ ይህ ቡድን በእምቢተኝነቱ ከቀጠለ እና ሰራዊታችን በሚያደረገው ህግን የማስከበር ዘመቻ የህዝብ መገልገያ ተቋማት፣ ቤተ እምነቶችና በመሳሰሉት ላይ ጉዳት ሊደርስ ይችላል፡፡ ምክንያቱም ጦርነት ነውና፡፡

ስለዚህ በየቀኑ የሃሞት ጽዋዉን እየተጎነጨ ያለውን ፅንፈኛውና አምባገነኑ የህወኃት ቡድን የመጨረሻ ዕድሉን ተጠቅሞ እጁን መስጠት ካልቻለ ከዚህም በላይ በቁሙ መራራ ጽዋ መጎንጨቱ አይቀሬ ነው፡፡ በየትኛውም ሁኔታ ከህግ ተጠያቂነት ሊያመልጡ የሚችሉበት ዕድል ዝግ ነውና፡፡  የጣት ቀለበት ያህል መፈናፈኛ እንኳ ማግኘት አይችሉም፣ ጁንታው ያለበት አካባቢ በሙሉ በጀግናው ሰራዊታችን ተከቧልና ፡፡

የትግራይ ህዝብ የህግ የበላይነት እንዲተገበር ሙሉ ፍላጎት እንዳለው ይታወቃል፡፡ ለዚህም ነው ሰራዊታችን ነጻ ባወጣቸው ከተሞች ያሉ ነዋሪዎች ድጋፋቸውን በተለያዬ መንገድ እያሳየ ያለው፡፡ ጁንታው የህወኃት ቡድን አካባቢያችሁን ከጠላት ጠብቁ በማለት ያስታጠቃቸውን ከቀላል መሳሪያ ጀምሮ እስከ ቡድን መሳሪያ ድረስ እኛ ጠላት የለንም እየሆነ ያለው ህግን የማስከበር ስራ ነው በሚል የተቀበሉትን መሳሪያ ለሰራዊታችን እያስረከቡ ያሉት፤ ከዚህ በላይ አጋርነት ምን አለ?

ስለሆነም ሰላም ፈላጊው የትግራይ ህዝብ ሆይ ቤተ እምነቶችን ጨምሮ በተለያዩ አካባቢዎች የመሸጉ ጸረ ህዝብ ሀይሎች ለዓመታት ቋጥኙን መንጥረህ፣ ተራራውን ንደህ የሰራሀውን መንገድና ድልድይ ከእናንተው ጉያ በተደበቁ ጥቂት አምባገነን ሀይሎች ትዕዛዝና በጀሌዎቻቸው አማካኝነት ጉዳት እየደረሰባቸው ይገኛልና ነጻ ሊያወጣህ ከሚታትረው ሰራዊታችን ጎን በመሰለፍና እነዚህን ጁንታዎች አሳልፈህ በመስጠት በደማቁ የሚጻፍ ታሪክ ትሰሩ ዘንድ ጊዜው አሁን ነው ፡፡

ድል ለሰራዊታችን !

Leave a Reply