You are currently viewing ትግራይን አኬልዳማ የማድረግ የጁንታው ሴራ

ትግራይን አኬልዳማ የማድረግ የጁንታው ሴራ

  • Post comments:0 Comments

ዮሐና ማርካን

የህወሓት አጥፊ ቡድን ለዓመታት የህዝብ ሃብት ሲመዘብር፣ ኢ-ሰብዓዊ የሆነ ድርጊት ሲፈጽምና የራሱን ኪስ ሲያደልብ ኖሮ ዛሬ የግፍ ጽዋው ሞልቶ ሲፈስ በስሙ ከመነገድ ውጭ ምንም ያልፈየደለትን የትግራይን ህዝብ መሸሸጊያው አድርጓል፡፡ የእኩይነቱ ጥግ የትግራይ ህዝብ ከሌላው የአገሪቱ ህዝብ ጋር በፍቅር ኖሮ ሳለ እንደተወረረ እንደተከበበ አድርጎ ፕሮፓጋንዳ በመስራት ለስደት እየዳረገውና ድርብ በደል እያደረሰበት ይገኛል፡፡

መንግስት ይህ የወንበዴ ቡድን ለዓመታት ምሽግ ውስጥ አገርና ህዝብ ለመጠበቅ የኖረው የአገር መከላከያ ሰራዊት ላይ የፈጸመው የውንብድና ተግባር መቼም ይቅር የማይባል እንደሆነ ግልጽ ነው፡፡ ይህ አለም የሚያውቀው እውነታ ሆኖ ሳለ ዛሬም ይህን እኩይ ተግባሩን ለመሸሸግ ትግራይ ተወራለች፣ ንጹሃን እየተገደሉ ነው በሚል ፕሮፓጋንዳ እየነዛ ይገኛል፡፡ ወትሮም በማንአለብኝነት የፈጸመው አሳፋሪ ድርጊት በመሆኑ ዛሬ ስቦ ወደጦርነት ያስገባውን መንግስት ዞሮ ሲከስ እንደማየት አሳፋሪ ነገር የለም፡፡  

ይህ እኩይነቱ ሳያንሰው መንግስት ህግና ስርዓት ማሰጠበቅ ላይ ብቻ ትኩረት በማድረግ በተጠና የወታደራዊ ስልት የማህበራዊ ተቋማትና የእምነት ተቋማትን በጠበቅ መልኩ የዚህ እኩይ ቡድን ለጥፋት ያዘጋጃቸው ቦታዎች ላይ እርምጃ እየወሰደ ይገኛል፡፡ ሆኖም ይህ ቡድን የማህበራዊ ተቋማትና የእምነት ተቋማትን የመሳሪያ መሸሸጊያ በማድረግ መንግስት ለሚወስደው እርምጃ ውንጀላ ለማቅረብ ሲዳክር ይውላል፡፡

መንግስት የጀመረውን ህግ የማስከበር እርምጃ የሚከፈለው መስዋዕትነት ተከፍሎ የሚጠናቀቅ እንጂ ወደኋላ የሚመለስ አለመሆኑን መገንዘብ ያስፈልጋል፡፡ መንግስት ስለአገር መስዋዕት በሆኑ ንጹሃን ደም የሚደራደር ደካማ አድርጎ ማሰብ የመንግስትን ዓላማ መሳት ብቻ ሳይሆን የመጨረሻው የጣር ጩኸት አድረጎ መረዳት ይገባል፡፡ ንጹሃን በጠራራ ጸሃይ ለማረድ፣ ለማሳረድ፣ አገር ለማፍረስ ያልራራ አካል ዛሬ በበወሬ ወለደ ታሪክ መንግስትን ለመወንጀል የቱንም ያህል ርቀት ቢኬድ ትርፉ መወራገጥ ነው፡፡

ይህ እውነታ እንዳለ ሆኖ መላው የአገራችን ህዝብ መገንዘብ የሚገባው ይህ ቡድን ዛሬም ለቁማሩ ማስያዣነት እየተጠቀመ ያለው ንጹሃኑን የትግራይን ህዝብ መሆኑን ነው፡፡  የእምነት ተቋማትን የመሳሪያ መሸሸጊያ ከማድረግ ጀምሮ የማህበራዊ ተቋማትን ጭምር ለእኩይ አላማው ማስፈጸሚያ የሚሆነውን የጦር መሳሪያ መሸሸጊያ አድረጓል፡፡ ይህ ዓላማው ግልጽ ነው፡፡ በመሆኑም መንግስት የሚወስደውን እርምጃ ወደኋላ የሚል ባለመሆኑ የትግራይ ህዝብ የዚህ እኩይ ቡድን ሴራን በመገንዘብና በማጋለጥ ራሱን ከጥፋት መጠበቅ ይገባዋል፡፡

ይህ ቡድን የኢትዮጵያዊ ስነልቦና የሌለው ከራሱ ፍላጎት ውጭ ማሰብ የማይችልና በታግዬልሃለሁ ሰበብ ህዝብን ባሪያ አድርጎ መኖር የሚሻ የወንበዴ ቡድን መሆኑን ከድርጊቱና ከመጣበት የጥፋት መንገድ መገንዘብ ይቻላል፡፡

አሁን የመጨረሻው እስትንፋሱ ላይ በመድረሱ ድርጊቱ ሁሉ በንጹሃን ደም መቆመር በመሆኑ መንቃት ይገባል፡፡ ስለነጻነት የማያወቀው ነፃነት አዋጁ የህወሓት ጁንታ ቡድን በኢትዮጵያውያን የጋራ ክንድ ድባቅ ይመታል፡፡ ይህ በቅርቡ የሚፈጸም እውነት መሆኑን በግልጽ መወቅ ይገባል፡፡

ድል ለመከላከያ ሰራዊታችን!

ምላሽ ይስጡ