You are currently viewing የሃሳብ ብዝሃነት የብልጽግና ፀጋ እንጂ እክል አይደለም

የሃሳብ ብዝሃነት የብልጽግና ፀጋ እንጂ እክል አይደለም

  • Post comments:0 Comments

በሚራክል እውነቱ

ከዴሞክራሲ ስርዓት መገለጫዎች መካከል አንዱ ሃሳቦችን በመደማመጥና በመከባበር መንፈስ በጠረንጴዛ ዙሪያ ማንሸራሸር መቻል ነው፡፡ የዴሞክራሲ ስርዓት ከእኔ ብቻ ልደምጥ ፍጹም የተለየ የብዙሃን ሃሳብ እንዲንሸራሸርና በዛም የተሻለው ሃሳብ የጋራ ሃሳብ ሆኖ እንዲወጣ እድል የሚሰጥ ስርዓት ነው፡፡ የግለሰብ ፍላጎትና አስተሳሰብን መሰረት ያደረገ አካሄድ ለዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ እንቅፋት ነው፡፡ ሀሳብ ሀብት ነው፤ በሀሳብ ውስጥ ሰላም፣ መተሳሰብ፤ መከባበር፣ አንድነት፣ አጋርነት እንዲሁም ብልጽግና አለ፤ይህ የማይካድ ሀቅ ነው፡፡የሁሉም ስራዎች መነሻ የሰዎች ሀሳብ ነው፡፡ ሰዎች ፈጣሪ በሰጣቸው አዕምሮ ተጠቅመው መልካም ነገሮችን ማፍለቅና ማምረት ሲጀምሩ ከእነሱ አልፈው ለህዝብና ለሀገር ጠቃሚ ሀሳቦችን ወደ ተግባር ይቀይራሉ፡፡ ብልጽግና ፓርቲ በመሰረታዊነት ከሚታገልባቸው ጉዳዮች መካከል አንዱ የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ነው፡፡ የሃሳብ ልዩነቶችን በመቻቻል ማስተናገድ ነው መርሁ ነው፡፡ ብልፅግና በሀሳብ ልዕልና የሚያምን ፓርቲ ስለሆነ ብቻ አይደለም ለዴሞክራሲ ትኩረት የሚሰጠው፤ ይልቁንም በሀሳብ ፍጭት ውስጥ የዳበረና ለሀገር ብልጽግና የሚጠቅም ውጤት ስለሚገኝ እንዲሁም ባለንበት በ21ኛው ክፍለ ዘመን የሃሳብ ልዩነት ካላስተናገዱ ለመንግሥት ቁመና የሚመጥን አስተሳሰብ ማዳበር ላይ ክፍተት እንደሚፈጠር ስለሚረዳ እንጂ፡፡በዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ የሃሳብ ብዝሃነት የብልጽግና ፀጋ እንጂ እክል እንዳልሆኑ ብልጽግና ፓርቲ ከልብ ይረዳል፡፡ ለመሆኑ ምን ያህሎቻችን የሃሳብ ልዩነቶችን ባለማክበራችን የተነሳ በዴሞክራሲ ሥርአት ግንባታ ላይ መግባባት እንዳይፈጠር እንቅፋት እንደሆንን እንረዳ ይሆን? መልሱን ለእናንተው ትቼ በእኔ የግል መረዳት የሀሳብ ብዝሃነትን በሚፈለገው ደረጃ ማስተናገድ ባለመቻሉ ችግሩ ተጠራቅሞ ዛሬ የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታው ላይ የራሱ የሆነ ጫና ሊያሳድር ችሏል፡፡ በሀገራችን በሀሳብ ልዕልና ወይም በዴምክራሲ ሥርዓት ግንባታ ላይ የጋራ መግባባት ተፈጥሯል ለማለት ቢከብድም ሁሉም ሰው የኢትዮጵያን ሰላምና አንድነት፣ ልማትና ዕድገት፣ብልጽግናና አንድነቷ የጠነከረ እንዲሆን ፍላጎት አለው፡፡ ፍላጎቱ እንደተጠበቀ ሆኖ ለዴሞክራሲያው ስርዓት ግንባታ መዳበር ሁሉም የራሱን ድርሻ ሊወጣ ይገባል፡፡ የጋራ መግባባት የሌለበት ማንኛውም እንቅስቃሴና ዕርምጃ ደግሞ ውጤቱ የከፋ ነው በመሆኑ መግባባትና ወንድማማችነትን አጣምሮ ማስኬድ ይገባል፡፡ ባለፉት ሁለት ዓመታት በመንግሥት በኩል የተወሰዱ ዕርምጃዎችም መንግስት የዳበረ የዴሞክራሲ ስርዓት ለመገንባት ካለው ፍላጎት መሆኑን ግልጽ ነው፡፡ የፖለቲካ እስረኞችን ከእስር መፍታት፣ በውጭ ይኖሩ የነበሩትንም ወደ ሀገራቸው ተመልሰው ትግል እንዲያደርጉ ማድረግ፣ ሀሳብን በነጻነት የመግለጽና ሌሎችም የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታን ለማጠናከር የተወሰዱ ዕርምጃዎችን ማንሳት ይቻላል፡፡ ብልጽግና እንደ አንድ መንግስት እንደሚመራ የፖለተካ ድርጅት በአገሪቷ የዳበረ የዴሞክራሲያዊ ስርዓት እንዲያብብ ፍላጎት ያለው በመሆኑ ይህ በሚፈለገው ደረጃ እስኪደርስ ድረስ የእለተ ተእለት ስራው አድረጎ የሚተገብረው ይሆናል፡፡ ለዴሞክራሲያዊ ሥርአት ግንባታ ወሳኙ የሆኑ ተቋማት ግንባታም ወሳን መሆናቸውን ይታመናል፡፡ ለዚህም በሥነ ምግባር የታነጸ ትውልድ ለመቅረጽ በሀገሪቱ የትምህርት ሥርዓት ውስጥ ተቀርጾ ተግባራዊ እየሆነ ያለውን የሥነ ዜጋና ሥነ ምግባር ትምህርትና ያለውን አበርክቶ እየመዘነ መሄዱ አስፈላጊ ነው የሚል እይታ አለኝ፡፡ ሃምሳ ሎሚ ለአንድ ሰው ሸክሙ ….እንደሚባለው መንግስትና መንግስትን የሚመራው ፓርቲ ብቻውን የሚያደርገው ሩጫ አድካሚ ይሆናልና ምሁራን፣ ፖለቲከኞች፣ ሁሉም የህብረተሰብ ክፍል መደማመጥ፣ መቻቻልና የሃሳብ ብዝሃነትን ማስተናገድ ባህሉ በማድረግ አገርን ማሻገር ይገባል ባይ ነኝ፡፡ ሰላም፡፡ ሰላም ለሀገራችን !ጤና ለህዝባችን !

ምላሽ ይስጡ