የብልጽግና እያንዳንዱ እርምጃ ትርጉም ያለውና ከመዳረሻችንና ከመንገዳችን ጋር ፍጹም የተቆራኘ ነው፡፡

የብልጽግና እያንዳንዱ እርምጃ ትርጉም ያለውና ከመዳረሻችንና ከመንገዳችን ጋር ፍጹም የተቆራኘ ነው፡፡

  • Post comments:0 Comments

ዮሐና ማርካን

መንግስት የአገራችንን ብልጽግና ለማረጋገጥ የሚያግዙ ማናቸውንም እርምጃዎች ከመውሰድ ወደኋላ እንደማይል በተደጋጋሚ አስረግጦ አስረድቷል፡፡ በተግባርም እያሳየ ይገኛል፡፡ ሰሞኑን ከገንዘብ ኖት ጋር ተያይዞ የወሰደው እርምጃም ይህን አቋሙን ያረጋገጠበት ወሳኝ ምዕራፍ ተደርጎ መውሰድ ይገባል፡፡ የብር ኖቶቹ መቀየር የሚያበረክተው ኢኮኖሚያዊ ፋይዳ እንደተጠበቀ ሆኖ በብር ኖቶቹ ላይ የተቀመጡት ምስሎች ደግሞ የላቀ ትርጉም ያዘሉ ናቸው፡፡

በአገራችን ታሪክ በተለያዩ ጊዜያት የወረቀት ገንዘቦች ለውጥ ተደርጓል፡፡ በአጼ ኃይለ ስላሴ የስልጣን ዘመን አራት ጊዜ ያህል የብር ኖቶች የተለወጡ ሲሆን በወታደራዊው ደርግ ዘመነ መንግስት በ1969 ዓ.ም ደግሞ የንጉሱን ምስል የያዙት የወረቀት መገበያያ ገንዘቦች ተለውጠዋል፡፡

በተመሳሳይም ኢህአዴግ ወደስልጣን ከመጣ በኋላ ለጥቂት ዓመታት በደርግ ጊዜ የነበረው የብርውን ኖት ሲጠቀም ቆይቶ ከኢትዮጵያና በኤርትራ መካከል ከተደረገው የድንበር ጦርነት በኋላ የብር ኖቶቹ እንዲቀየሩ አድርጓል። በአጠቃላይ ከአጼ ኃይለስላሴ ዘመነ መንግስት ጀምሮ አገልግሎት ላይ ይውሉ የነበሩት የገንዘብ ኖቶች 100፣ 50፣ 10፣ 5፣ 1 ብር ሆኖ ዘልቋል፡፡ ባሳለፍነው ሳምንት በአገራችን ለመጀመሪያ ጊዜ ተግባራዊ የተደረገውና የሰላም ምልክት የሆናችውን እርግብ ምስል የያዘው የ200 ብር ኖት በአዲስ መልክ የታተመና የብዙ ሰዎችን ትኩረት እንደሰባ መገንዘብ ይቻላል፡፡

ብልጽግና ባለፉት ዓመታት በአገሪቱ ያጋጠመውን መዋቅራዊ የኢኮኖሚ ስብራት ለመጠገን የተለያዩ እርምጃዎችን እየወሰደ ይገኛል፡፡ ባለፉት ዓመታት ሕጋዊ ከሆነ የገንዘብ ዝውውር ውጭ ኢ-መደበኛ በሆነ መንገድ የገንዘብ ዝውውር ሲካሄድ እንደነበረ በተለያየ ጊዜ ይፋ መደረጉ ይታወሳል፡፡ ባለፉት ሦስት ዓመታት ውስጥ በከፍተኛ ሁኔታ ሲዘዋወር የነበረውን ሕገወጥ የገንዘብ ዝውውር በተመለከተም በጉምሩክና በፖሊስ በኩል በተደጋጋሚ ሪፖርቶች ወጥተዋል፡፡ ይህ የአገሪቷን ኢኮኖሚ በመጉዳት ህዝባችን ላይ የሚያሳድረው ጫና ቀላል እንዳልሆነ መገመት አያዳግትም፡፡ ይህን ሁኔታ መንግስት ከመሰረቱ ለመቀየር ኢ-መደበኛ የሆነውን የገንዘብ ፍሰት ወደ መደበኛ ለማምጣት በርካታ ጥረቶች የተደረጉ ሲሆን በተለያየ ጊዜም የወጡ መመሪያዎችም ተጨባጭ ማሳያዎች ናቸው።

3.7 ቢሊዮን ብር የህትመት ወጪ የወጣበት ይህ የብር ኖት ታዲያ ከባንክ ውጭ በከፍተኛ ሁኔታ ይንቀሳቀስ የነበረውን የብር ኖትና ከዚህ ጋር ተያይዞ የሚፈጠሩ ህገ ወጥ እንቅስቃሴዎችን ለመግታት የላቀ ሚና አለው፡፡ አገሪቱ ከፍተኛ የሆነ የጥሬ ገንዘብ እጥረት (ሊኩዊዲቲ) አጋጥሟት የነበረበት መሰረታዊ መነሻም ከባንክ ውጭ የሚንቀሳቀሰው ጥሬ ገንዘብ መሆኑ ግልጽ ነው፡፡ ከባንክ ውጭ የሚደረግ ግብይት ባንኮችን ለጥሬ ገንዘብ እጥረት እንዲጋለጡ ያደርጋል፡፡ ከባንክ ውጭ የሚንቀሳቀስ ገንዘብ ለሕገ ወጥ ተግባራት ይውላል፡፡ በጥቅሉ ከባንክ ውጭ ኢመደበኛ በሆነ መልኩ የሚንቀሳቀስ ገንዘብ አገራዊ ፋይዳ አይኖረውም፡፡

በጥቅሉ የብር ኖቱ መቀየር መንግስት እየገነባ ያለውን ጠንካራ የኢኮኖሚ መዋቅር በማሳየት ህዝቡ ከዚህ ቀደም ያጣውን እምነት መልሶ ለመገንባት እድል ጭምር የሚሰጥ ነው፡፡ የለውጥ ኃይሉ ወደ ስልጣን ከመጣ በኋላ የተለያዩ ወገኖች የብር ኖት ለውጥ ጥያቄ ዋነኛው እንደነበረ ይታወሳል፡፡

በምክነያትነት የሚጠቀሰው ደግሞ በሕገ ወጥ መንገድ የሚንቀሳቀሰውን ገንዘብ ስርዓት እንዲበጅለትና አገሪቷ ውስጥ ጤናማ የኢኮኖሚ ስርዓት እንዲፈጠር ነው፡፡ ይህ ወሳኝ እርምጃ የአገራችንን ኢኮኖሚ ለማወክ ቀን ከሌሊት ስራዬ ብሎ የሚራወጠውን ኃይል ጫና ከመቀነሱ ባሻገር ሕጋዊ ባልሆነ መንገድ የሚንቀሳቀሰው ገንዘብ የወንጀል ማስፈጸሚያ መሆን የሚችልበት እድል ዝግ እንዲሆን ያደርጋል፡፡

የብልጽግና ራዕይና የኢትዮጵያዊነት እውነት የተገለጠበት የብር ኖት
ብብር ኖቶቹ ላይ የሰፈሩት ምስሎች እንደብዙዎቻችሁ የእኔንም ቀልብ ይዘውታል፡፡ እናም በብር ኖቶች ላይ የሰፈሩትና ምስሎች ትርጉማቸው ጥልቅ ነውና መረዳቴን እንዲህ ላጋራችሁ፡፡
50 ግብርና እና ኢንዱስትሪን አጣምሮ የያዝ ምስል ይዟል ይህ ደግሞ ግብርና የአገራችን ኢኮኖሚ የጀርባ አጥንትና የኢንዱስተሪ ሽግግራችን መሰረት መሆኑን የሚያመላክት ነው፡፡ ሁለቱም በአንድ ኖት በሁለት ገጽ በአንድ ላይ ሰፍረዋል፡፡ መነሻችንና መዳረሻችን ሁለቱም በአንድ ገፅ ለብልጽግናችን መሰረት እንደሆኑ በግልጽ ያመላክታል፡፡
100 ብሩ ላይ የታተሙት ምስሎችም አስተውሎ ላያቸው ስብጥራቸው ኢትዮጵያዊነትን በእጅጉ አጉልቶ የሚያሳይ ነው፡፡ አገራችን ኢትዮጵያ የብዙ ሺ ዘመን ታሪክ ያላት ጥንታዊት አገር መሆኗን የሚያመላክትና የብዝሃነት ምልከት መሆኗን የሚያንፀባርቅ ነው፡፡ አክሱም፣ የፋሲል ግንብ፣ ጀጎል…ሶፉመር ዋሻ በአንድ ሰድሮ የያዘ ነው፣ ከመገበያያነት ባለፍ ወደራሳችን ተጠግተን እንድናስብ የሚጋብዝ ጭምር ነው፡፡
10 ብር ላይ የተቀመጠው የግምለ ምስል ትርጉም ጥልቅ መሆኑን መገንዘብ ያስፈልጋል፡፡ ኢትዮጵያ የሁላችንም መሰብሰቢያ አገር፣ አርብቶና አርሶ አደሩ በአንድ ባንዲራ ስር ለብልፅግናዋ የሚዋደቁላት አገር መሆኗን የሚገልጽ ነው፡፡ አገራችንን እጅ ለእጅ ተያይዘን በአንድ ሞሰብ ተቋድሰን ተዋደንና ተከባብረን ወደፊት የምናሻግራት የጋራ ሃብታችን መሆኗንም በጉልህ ያሳያል፡፡
የ200 ብር ኖቱም የብሩህ ተስፋና የሰላም ምልክት የሆነችውን ርግብ ምስል ይዞ በአዲስ መልክ ገበያውን ተቀላቅሏል፡፡ የአገራችን ኢኮኖሚ ፍትሃዊነት የሰፈነበት የተረጋጋና አገራችንን ወደ ብልጽግና የሚያሻግር እንዲሆን እጅ ለእጅ ተያይዘን በሰላም በፍቅር በወንድማማችነት ስሜት የምንጓዝበት የድል ዓመት እንዲሆን ተመኘሁ፡፡ ሰላም፡፡

Leave a Reply