ጽንፍ ላይ ያለው መጫወቻ ሜዳ ጠባብ ነው

ጽንፍ ላይ ያለው መጫወቻ ሜዳ ጠባብ ነው

  • Post comments:0 Comments

በአብዲ ኬ…

የሰው ልጅ እንደመልኩ በሃሳብም የተለያየ ነው፡፡ የአለም ህዝብ፣ በቆዳ ቀለም የሚመሳሰሉ፤ የአንድ አህጉር ወይም የአንድ አገር ልጆች፤ የአንድ ብሄር ተወላጅ ይቅርና የአንድ እናት ልጆች አለፍ ሲል መንታ ወንድማማቾች ጭምር በአስተሳሰብ ሰፊ ልዩነት ይኖራቸዋል፡፡ይህ የአለም እውነታ ነው፤ በሃሳብ መለያየት ደግሞ ለአለማችን ጸጋ እንጂ እርግማን አይደለም፡፡ እንኳን ሁሉም አንድ ነገር ማሰብ፤ አንድን ነገር እራሱ በተለያየ መልኩ ማሰብ ባይኖር ኖሮ የሰው ልጅ ዛሬ አዳዲስ ነገሮችን እየፈጠረ አለምን ቀይሮ በቁጥጥሩ ስር አድርጎ ወደ ህዋ ማምጠቅን ብሎም ማርስ ላይ መኖርን ባላሰበ ነበር፡፡የሃሳብ ልዩነት ጸጋ የሚሆነው ታዲያ፤ የሃሳብ ልዩነት ማለት አማራጮች የሚሰፉበት የሰው ልጅ በተፈጥሮ የተቸረ፤ ከሌሎች እንስሳትም የሚለይበት አንዱና ትልቁ በረከት መሆኑን ስንገነዘብ ነው፡፡ለምን እንደኔ አታስብም፤ የኔን አስተሳሰብ ለምን አትከተልም፤ ለምን ከኔ የሚቃረን ወይም የኔን ሃሳብ የሚሽር ነገር አመጣህ ከተባለ ግን፤ ጸጋነቱና ለአገርና ለአለም በረከት መሆኑ ቀርቶ የልዩነትና አለመግባባት መነሻ ነው የሚሆነው፡፡የኔ/ የኛ ሃሳብ ትክክል ይሆን ዘንድ የሱ/ የእነርሱ ስህተት መሆኑን አለበት ወደሚለው ጽንፍ የረገጠ ተቃርኖንም ያስከትላል፡፡ ይህ ሲሆን ማየት ደግሞ እንግዳ ክስተት አይደለም፡፡ በተለይ በፖለቲካው አለም/ በተለይ ዴሞክራሲ ካልዳበረበት የፖለቲካ ልምምድ ከባቢ ውስጥ ለአንድ አላማ፤ ለአንድ ህዝብና አገር እየታገሉ፤ እንዴት ቢሰራ ወይም በምን አይነት መልኩ እንታገል የሚል የአስተሳሰብ ልዩነት በጠላትነት ሲያፈራርጅ ማየቱ እንግዳ ነገር አይደለም፡፡ ከዚያም አልፎ አንድ ወይም ሁለት ጉዳይ ላይ የሃሳብና የአካሄድ ልዩነት ተፈጠረ ተብሎ ሌላው ሰፊ ነገር ወይም ትልቁ አላማ ተረስቶ በጠላትነት መፈራረጅ ከዚያም አለፍ ሲል መጠፋፋት የፖለቲካው አለም ላይ የተለመደ ክስተት ነው፡፡ይህ ደግሞ ጽንፍ የያዘ አስተሳስብ ውጤት ነው፡፡ጽንፍ የያዘ አስተሳስብ፤ ሁለተኛ አማራጭ የማያስቀምጥ፤ የሌላውን ወገን እውነታ ለመስማት በር የማይከፍት አካሄድ፤ እኛና እነሱ የሚል መከፋፈልን ማስከተሉ ስለማይቀር እኔ ያልኩት ካልሆነ ሁሉ ነገር አይሆንም፤ አንተ/ እኛ ጋር ትክክል የሆነ ነገር እሱ ወይም እነርሱ ጋር ስህተት ነው፤ እነርሱ ጋር ስህተት የሆነ ደግሞ እኛ ጋር ትክክል ነው የሚል የመቃረን አባዜንም ይዞ ይመጣል፡፡ የተካረረ ገመድ ጉተታ ውስጥም ያስገባል፡፡ የከረረ ነገር ደግሞ መርገብ አለበት ካልሆነ መበጠሱ ስለማይቀር በሁለቱም ወገን ገመድ ጉተታ ላይ የተሳተፉ ወገኖች መጎዳታቸው አይቀርም፡፡የገመድ ጉተታዎቹ ወደ ኋላ መውደቅ ደግሞ አገርና ህዝብ ይጎዳል፡፡ጉዳት ሲባል ታዲያ እንዲህ ቀላል ጉዳት አይደለም አገርን ላለመረጋጋት፤ ለመፍረስ አደጋ የሚያጋልጥ ነው፡፡ ለዚህም ነው ብልጽግና አምርሮ ከሚታገልባቸው አጀንዳዎች መካከል አንዱ ዋልታ ረገጥነት ወይ ጽንፈኝነት መሆኑን በግልጽ የሚያስቀምጠው፡፡ በርግጥ ብልጽግና ጭቆናን፤ አቅላይነትን፤ ሌብነት፤ ጊዜ ታካኪነትንና ልግመኝነትንም አምርሮ ይታገላቸዋል፡፡ ቀሪዎቹን የትግል አጀንዳዎች በሌሎች ጽኁፎች ለመዳሰስ ሞክራለው፡፡ዋልታ ረገጥነትን መታገል ለምን ቀዳሚ የብልጽግና አጀንዳ ሆነ ካላችሁኝ አገራችን ውስጥ ያሉ ጽንፍ የረገጡ አስተሳሰቦችና የመቃረን አባዜዎች ለአገር ህልውና አደጋ ናቸዉ ብሎ ስለሚያምን ነው፡፡ በተለይ ከብሄር ማንነትና አገራዊ አንድነት መካከል ያለው ለመታረቅ ዝግጁ ያልሆኑ ጽንፍ የረገጡ አካሄዶች፤ ታሪክ ላይ ያለን አተያይና የታሪክ ትርክቶች እንዲሁም የአገር ምልክት የሆነው ሰንደቅ አላማ ላይ ያሉ አለመግባባቶች፡፡እነዚህን ሃሳቦች የሚያራምዱ ጽንፍ አስይዞ የሚያካርሩ፤ ትልቁን የጋራ አጃንዳችን ወደ ጎን ትተው ገመድ ጉተታ ውስጥ የገቡ ሰዎች ወይም ቡድኖች ጥቂት ናቸው፡፡ አብዛኛው ዜጋ ደግሞ ህዝብ የሚያስታርቅ ሃሳብ የሚሻ መግባባትን አጥብቆ የሚመኝ፤ ከመግባባት ውስጥ የሚገኝ የሰላምና መረጋጋት ትሩፋትንም የሚናፍቅ ነው፡፡በመሆኑን ብልጽግና በሁሉም ነገር ላይ የመሃል ፓለቲካ አራማጅ ወይም *ሴንቴሪስት* እንደመሆኑ ከጽንፍ የጸዳ ነው፡፡ ተግባር ተኮር ሆኖ፤ ለአገርና ህዝብ የሚጠቅሙ እውነቶችና እውቀቶችን ብቻ ነው የሚቀበለው፡፡በመሆኑም የአገሪቱን ኢኮኖሚያዊ እድገትና የዴሞክራሲ ችግሮች ለመፍታት መካረሮች መሃል ሚዛን በማስጠበቅ በዚያውም ከሁለቱም ጽንፍ የፀዳ ሰፊውን ህዝብ አቅፎ መሄድን አማራጩ አድርጓል፡፡እኔም እላችኋለው፤ ጠባቡን ጽንፍና ጽንፍ ትተን ሰፊው መሃል ላይ እንጫወት፡፡ ጽንፈኞች የሚጓታቱበት የተካረረውን ገመድ በማርገብም ህዝባችንና አገራች ከጥፋት እንታደግ፡፡ የቁልቁለት ጉዞዓችንም አብቅቶ ወደ ከፍታ ሰፊውን ህዝብ ይዘን ጉዞ እንጀምር፡፡

Leave a Reply