በዘንድሮ የአረንጓዴ አሻራ የችግኝ ተከላ መርሃ ግብር እስካሁን ከእቅዱ 83 በመቶ መከናወኑ ተገለፀ።
“የአረንጓዴ አሻራ” የክረምት የችግኝ ተከላ መርሃ ግብር አፈፃፀም ግምገማ በዛሬው እለት ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ በተገኙበት ተካሂዷል።
በዚህ መድረክ ላይም የግብርና ሚኒስትር አቶ ኡመር ሁሴን ባቀረቡት ሪፖርት፥ በዘንድሮው የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር እስካሁን ከ4 ቢሊየን 156 ሚሊየን በላይ ችግኝ መተከሉን አስታውቀዋል።
እስካሁን የተተከለው ችግኝ በዘንድሮው “የአረንጓዴ አሻራ” የችግኝ ተከላ መርሃ ግብር ለመትከል ከተያዘው እቅድ ውስጥ 83 በመቶ መሆኑንም ነው የገለፁት።ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ በዚሁ ወቅት፥ የዘንድሮው “የአረንጓዴ አሻራ” እቅድ የእስካሁን አፈፃፀም በጥሩ ሁኔታ ላይ እንደሚገኝ አስታውቀዋል።
ቀሪ ጊዜያት እያሉ የችግኝ ተከላው በ83 በመቶ መሳካቱ የተያዘው እቅድ እና ዝግጅት ውጤታማ እንደነበረ የሚያመላክት መሆኑንም አስታውቅዋል።እስካሁን በተሰራው ስራ አፈፃፀሙ ጥሩ ቢሆንም፤ እቅዱን ሙሉ በሙሉ ለማሳካት በቂ ትኩረት ንደሚያስፈልግም ነው ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ የተናገሩት።
የአረንጓዴ አሻራ ጉዳይ የመንግስት ተቋማትና የስራ ሃላፊዎች ዋነኛ ስራ ሊሆን እንደሚገባ በማንሳት፤ የችግኝ ተከላ መርሐ ግብሩ ከኢኮኖሚያዊ ጥቅም እና ከሥራ ፈጠራ ጋር ማያያዝ እንደሚገባም ነው ያሳሰቡት።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አክለውም፥ ክልሎችም በቀሪ 1 ወር ጊዜ ውስጥ እቅዳቸውን ከማሳካት በተጨማሪ በሙሉ አቅማቸው ተከላው ላይ እንዲሰሩም ጠይቀዋል።
የ2013 “አረንጓዴ አሻራ” የችግኝ ተከላ መርሃ ግብር ለ3ኛ ዓመት የሚደረግ በመሆኑ ከኢትዮጵያ አልፎ በጎረቤት ሀገራትም እንዲካሄድ መታሰብ አለበት ብለዋል።
ኢትዮጵያ የምስራቅ አፍሪካ ሀገራት ቀጠናን አስተባብራ እንደምትሄድ ሀገር በአፍሪካ ግንባር ቀደም ስራ መስራት እንዳለባትም አስታውቅዋል።
ለዚህም ለቀጣይ ዓመት ለጎረቤት ሀገራትም በሚሊየን የሚቆጠሩ ችግኞች እንዲዘጋጅም ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሳስበዋል።