You are currently viewing የታላቁ የህዳሴ ግድብ የመጀመሪያ ዙር የውሃ ሙሌት ተጠናቀቀ

የታላቁ የህዳሴ ግድብ የመጀመሪያ ዙር የውሃ ሙሌት ተጠናቀቀ

  • Post comments:0 Comments

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 15፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የኢትዮጵያ ታላቁ የህዳሴ ግድብ የመጀመሪያ ዙር የውሃ ሙሌት መጠናቀቁን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ አስታወቁ።

የጠቅላይ ሚኒስትር ፅህፈት ቤት የአፍሪካ ህብረት ዓባላት ቢሮ መሪዎች በህዳሴ ግድብ ዙሪያ ያካሄዱትን ውይይት አስመለክቶ መግለጫ አውጥቷል።

በመግለጫው በቀጣናው የታየው ወቅታዊ የዝናብ እና የፈሰስ መጠን መጨመር ግድቡን ለመሙላት ሁኔታዎችን አመቺ አድርጓል፡፡

የግድቡን የመጀመሪያ የውኃ ሙሌት እና ዓመታዊ የሥራ ክንውን አስመልክቶ፣ ኢትዮጵያ ሚዛናዊ እና ሦስቱም ሀገራት በፍትሐዊነት ከ ዓባይ ወንዝ እንዲጠቀሙ የሚያስችል ድርድርን ለማካሄድ ባላት አቋም ትቀጥላለች ብሏል ፅህፈት ቤቱ።

ባለፉት ሁለት ሳምንታት ከተገኘው ከፍተኛ የዝናብ መጠን የተነሣ፣ የግድቡ የመጀመሪያ ዓመት የውኃ ሙሌት ተጠናቋል ያለው ፅህፈት ቤቱ ውኃው በግንባታ ላይ ያለውን ግድብ አልፎ እየፈሰሰ እንደሚገኝ አስታውቋል።

በትናትናው ዕለት የተካሄደውን የወቅቱ የአፍሪካ ህብረት ሊቀ መንበርና የደቡብ አፍሪካ ፕሬዚዳንት ስሪል ራማፎሳ በቪዲዮ ኮንፈረንስ የተካሄደውን ስብሰባ መርተውታል።

በስብሰባው ላይም የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ፣ የሱዳን ጠቅላይ ሚኒስትር አብደላ ሀምዶክ እና የግብፅ ፕሬዚዳንት አብዱልፈታህ አልሲሲ ተሳትፈዋል።

በተጨማሪም የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን ሊቀ መንበር ሙሳ ፋቂ መሃመትን ጨምሮ የቢሮው አባላት የሆኑት የኬንያ፣ የዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ እና የማሊ ሀገራት መሪዎች እና ተወካዮችም ታድመዋል።

ውይይቱን ተከትሎም ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ፥ በደቡብ አአፍሪካው ፕሬዚዳንት ስሪል ራማፎሳ አመቻችነት ለአፍሪካዊ ችግር አፍሪካዊ መፍትሄ የሚለውን ለማጠናከር ፍሬያማ ውይይት አካሂደናል ብለዋል።

በግድቡ ውሃ አሞላል ዙሪያም ቴክኒካዊ ውይይቶችን ቀጥሎ ለማካሄድ የጋራ መግባባት ላይ ለደረሱት የሱዳን ጠቅላይ ሚኒስትር አብደላ ሀምዶክ እና ለግብፅ ፕሬዚዳንት አብዱልፈታህ አልሲሲም አድናቆታቸውን ገልፀዋል።

ምላሽ ይስጡ