ፓርቲያችን ብልፅግና ከለውጡ ማግስት ጀምሮ በልዩ ትኩረት እየከወናቸው ከሚገኙ ጉዳዮች መካከል በቀደምት ሀገረ መንግስት ግንባታ ታሪኮቻችን ውስጥ የንትርክ እና የቁርሾ መንስኤ ሆነው በሁሉም ዘንድ ቅቡልነቱ የተረጋገጠ መንግስታዊ ስርዐት እንዳይኖረን ልዩነቶቻችንን ያሰፉ ጉዳዮችን ነቅሶ በማውጣት እልባት መስጠት ነው፡፡
በዚህ ረገድ ሀገራችን ኢትዮጵያ ብዝሀነትን እና ህብረ ብሔራዊ አንድነትን አሰናስሎ በመጓዝ ዙሪያ ገጥመዋት ለነበሩ ተግዳሮቶች መፍትሄ ለመስጠት የሄድንበት ርቀት በግንባር ቀድምትነት የሚጠቀስ ጉዳይ ነው፡፡
በዘመናዊ ሀገረ መንግስት ግንባታ ታሪካችን ውስጥ እንደ ሀገር ከፈተኑን ጉዳዮች መካከል ተፈጥሯዊ የሆነውን የብዝሀነት ጥያቄን በማስተናገድ ረገድ የገጠሙን ፈተናዎች ቀላል አልነበሩም፡፡
ኢትዮጵያ ቀለመ ብዙ ሀምራዊት ሀገር መሆኗን የዘነጋው የቀደምት ሀገረ መንግስት ግንባታ ጥረታችን፤ በውስጣችን ያሉ ተፈጥሯዊ ልዩነቶች ውበት እንደሆኑ በውሉ እውቅና ያልሰጠው ፍኖተ ጉዟችን፤ ሀገራችን በበርካታ ውስብስብ ችግሮች እንድትተበተብ ብሎም በትውልድ እልፍ አእላፍ ትግሎች እና መስዋዕትነቶች ተገንብቶ የማያላቅ ውዝፍ የቤት ስራ እንድንሸከም አድርጎናል፡፡
በዘመናት መካከል ጥያቄዎች ሲነሱ፤ አብዮቶች ሲፈጠሩ ወይም የምንፈጥራቸው ስርአተ መንግስቶች ሲናጉ ሁነኛ የለውጥ እና የትግል ሀሳብ ማጠንጠኛ ሆኖ የሚነሳው ብዝሀነትን ማዕከል ያደረገው ጥያቄ ነው፡፡ ተፈጥሯዊ ማንነቴን አክብሩ፤ፍትሀዊነትን አስፍኑ፤በወል ማንነቶች ግንባታ ጉዟችሁ መለያ ማንነቴን አትርሱ የሚሉ ትግሎች ፍሬ ያፈሩ ዘንድ እንደ ሀገር የከፈልነው ዋጋ ቀላል የሚባል አልነበረም!
ይህንን በውል የተደረዳው ፓርቲያችን ብልፅግና ከለውጡ በኋላ በመደመር እሳቤ የቀየሰው ሀገራዊ መንገድ በሀገራችን ውስጥ ያሉ ማንነቶች ተፈጥሯዊ መሆናቸውን እውቅና የሰጠ፤ህብረ ብሔራዊ መሆናችን ሀብት እንጂ ስጋት እንዳልሆነ የተገነዘበ፤ኢትዮጵያዊነት የጋራ ማንነታችን እንደሆነ እና ፈፅሞ ከብሔረሰባዊ ማንነታችን ጋር ሊጣረስ የማይችል እንደሆነ ባመነ ጉዞ ነው፡፡
ይህንንም በሙሉ ቁመና ማረጋገጥ እንድንችል እና ጠንካራ፤ተሻጋሪ እና ቅቡልነቱ የፀደለ ሀገረ መንግስት ግንባታ ይኖረን ዘንድ ልንላበሳቸው የሚገቡ መርሆችን እንዳሉም በወል ተገንዝበን ዴሞክራሲያዊነት እንዲያበብ፤ተቋማዊነት እንዲጠናከር፤የወንድማማችነት እና የእህትማማችነት እሳቤ እንዲፈካ የሰራናቸው በርካታ ስራዎች ውጤት ማፍራት ችለዋል፡፡
ፓርቲያችን ብልፅግና ያለ ዴሞክራሲ ህብረ ብሔራዊ አንድነትን መፍጠር እንደማይቻል በአግባቡ ይረዳል፡፡ በህዝባችን ዘንድ ያሉ መሰረታዊ ጥያቄዎች ወደ አደባባይ ወጥተው ምላሽ ሊያገኙ የሚችሉት፤የፖለቲካ ነጋዴዎች የህዝብን ጥያቄ ተገን አድርገው የሚጠነስሱት እኩይ ሴራ ሊመክን የሚችለው ብሎም ቅቡልነቱ የተረጋገጠ እና ብዝሀነትን ማዕከል ያደረገ አሰባሳቢ ህብረ-ብሔራዊ አንድነት መፍጠር የምንችለው ዴሞክራሲን በሙሉ ቁመና ማረጋገጥ ስንችል በመሆኑ ለጉዳዩ ልዩ ትኩረት ሰጥተን በመንቀሳቀስ ላይ እንገኛለን፡፡
ይህም ጥረታችን ፍሬ ያፈራ ዘንድ ከፍተኛ አስተዋፆ እያበረከተ የሚገኘው የተቋማዊነት እሳቤ ነው፡፡ሁሉም የሀገራችንን ህዝቦች ለሚያነሷቸው ጥያቄዎች በዘለቄታዊነት መልስ መስጠት የምንችለው፤ተፈጥሯዊ የሆነ የብዝሀነት ውቅርናችን ፍሬ የሚያፈራው፤ እንዲሁም ለሁላችንም የምትሆን ሀገር መፍጠር የምንችለው ጉዟችን በተቋማዊነት እሳቤ ሲቃኝ እንደሆነ በአግባቡ ተረድተን የወሰድናቸው እርምጃዎች አመርቂ ውጤት አስመዝግበዋል፡፡
በድምሩም ወንድማማችነት እና እህትማማችነት የሚፈጥር፤በህዝቦች መሀል ያለው ትስስር የሚያጠናከር፤የአንዱ ህመም ለሌላው ህመም እንደሆነ በውል የሚገነዘብ፤ለጋራ ህልውና መረጋገጥ በጋራ መቆምን የመረጠ የፖለቲካ ስርአት መገንባት ችለናል፡፡
ውድ የሀገራችን ብሔሮች፤ብሔረሰቦች እና ህዝቦች..
ህብረ ብሔራዊ አንድነት ወደ ተሟላ የብሔራዊነት ትርክት የምንሻገርበት ድልድይ ነው! ህብረ ብሔራዊ አንድነትን መፍጠር ከቻልን መከባበር፤መቻቻል እና መተሳሰብ መርሁ ያደረገ ጠንካራ ትውልድን ማዋለድ እንችላለን፡፡
እንደ ብልፅግና ፓርቲ የምንረዳውና በሙሉ ቁመና ይረጋገጥ ዘንድ ትግል የምናደርግለት እውነታ ህብረ ብሔራዊነት ለኢትዮጵያ መፃኢ እድል የብርሀን መንገድ በመሆኑ ምክንያት ነው፡፡
በብዝሀነት ዙሪያ ለሚነሱ የውስጥ ችግሮቻችን እልባት ለመስጠት እንዲቻልም እንደ ፓርቲ የመረጥነው የመደመር እሳቤ ለችግሮቻችን በሙሉ ዘላቂ መፍትሄ እንደሚሰጥ ፈፅሞ ጥርጥር የለንም፡፡ ምክንያቱም መደመር ሀገር በቀል የሆነ እና ከእኛው ለእኛው የተቸረ እሳቤ፤ከእኛው ህመም ለእኛው የተቀመመ መድኒት በመሆኑ መሰል ችግሮችን የመፍታት አቅሙ ከፍተኛ ነው!
በህዝቦች ዘንድ የተመጣጠነ ውክልና ዳግም ጥያቄ እንዳይሆን፤ቀጣዩ ትውልድ ላለፉት 50 አመታት ስንዳክርባቸው በኖሩ ጥያቄዎች ዳግም እንዳይፈተን፤ብዝሀነታችን ፈፅሞ ፈተና እንዳይሆን በእስካሁኑ ጉዟችን ያገኘናቸው ወረቶች በማካበት እንዲሁም ያጋጠሙንን ፈተናዎች በማረም ለብሔራዊነት ትርክት ግንባታ በጋራ ልንንቀሳቀስ ይገባል፡፡
የህብረ ብሔራዊነት ምሳሌ በሆነችው በጅግጅጋ ከተማ 18ኛው የብሔሮች ብሔረሰቦች እና ህዝቦች ቀን በዓለንም ስናከብር ይህንን አሰባሳቢ ትውልድ ተሻጋሪ ትርክት ለመገንባት ጥረት በማድረግ ሊሆን እንደሚገባ ለማሳሰብ እንወዳለን፡፡
ብዝኃነትና እኩልነት ለሀገራዊ አንድነት መረጋገጥ ያለውን ፋይዳም በውል ተገንዝበን ለአንዲት ታፍራ እና ተከብራ ለምትኖር ሉዐላዊት ሀገር ግንባታ የበኩላችንን ድርሻ እንድንወጣ አደራ ማለት እንፈልጋለን፡፡
ብልፅግና ፓርቲ
ህዳር 29 2016 ዓ.ም