You are currently viewing ከሀይል የዘለለ የሉዓላዊነት ማሳያ…. /በሚራክል እውነቱ/

ከሀይል የዘለለ የሉዓላዊነት ማሳያ…. /በሚራክል እውነቱ/

  • Post comments:0 Comments
የመሠረት ድንጋይ ከተጣለበት እለት አንስቶ የኢትዮጵያ ብሄሮች ብሄረሰቦችና ህዝቦች በሁሉም የሃገሪቱ አቅጣጫዎች በርካታ የድጋፍ ሠልፎችን ከማካሄድ ጀምሮ ከልጅ እስከ አዋቂ፣ ከተማሪ እስከ ምሁሩ ድረስ ያለው በጉልበቱ፣ በገንዘቡና በዕውቀቱ ለመርዳት ቁርጠኝነቱን በተለያዩ አጋጣሚዎች ሲገልጽ መቆየቱ የሚታወቅና ምናልባትም አለምን ያስደመመ ሀገራዊ ፕሮጀክት ነው፡፡
 
ከድህነት መውጫ መንገዶች አንዱና ዋነኛው መሆኑን በመገንዘብ ኢትዮጵያዊያን ተሳትፏቸውን አጠናክረው ቀጥለውበታል። የአገሪቱን ኢኮኖሚ ወደ አንዱስትሪ ስለሚያሸጋግር ዜጎቿ ከዕለት ጉርሳቸው ቀንሰው ለማጠናቀቅ ከጊዜ ጋር እልህ ውስጥ ገብተዋል፤ይህ በኢትዮጵያዊያን ልብ ውስጥ ያለ የሁሉም ዜጎች አሻራ ያረፈበት ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ነው፡፡
 
ግድቡ ኢትዮጵያ ያላትን አካባቢያዊም ሆነ አህጉራዊ አቅም እንደሚያጠናክርና ብሔራዊ ክብሯን እንደሚያስጠብቅ አጥብቀን ስለምንረዳ ቀዳሚ ሀገራዊ አጀንዳችን አድርገን ይዘነዋል ። ግድቡ ለዜጎች ብሔራዊ ኩራት ከመሆኑም ባሻገር ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያና ፖለቲካዊ ፋይዳ እንዳለው ይታወቃል።
 
ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ኢትዮጵያዊያን ከድህነት ለመውጣት የሚያደርጉትን እልህ አስጨራሽ ትግል እውን ማድረጊያ ፕሮጀክት መሆኑን በውል ተረድተውታል።
ብልጽግና ፓርቲ በመጨረስ እንጂ በመጀመር አያምንም፡፡
 
በብዙ ቢሊዬን ብር ወጪ የተጀመሩና ታላቁን የህዳሴ ግድብ ጨምሮ በተለያዩ ጊዚያት በህዝብና በመንግስት የጋራ ትብብር በግንባታ ሂደት ውስጥ ያሉ በርካታ ሀገራዊ ፕሮጀክቶች እንዳሉ ይታወቃል፡፡
 
እነዚህ ፕሮጀክቶች በታቀደላቸው ጊዜ ተጠናቀው ቢሆን ኖሮ እንደ ሀገር የኢኮኖሚውን ከፍታ ከማሳደጋቸው በተጨማሪ ለሙስናና ለብልሹ አሰራሮች ባልተዳረጉ ነበር፡፡ ይህ ደግሞ መንግስት ተጨማሪ በጀት እንዲመድብ ያስገድደዋል፡፡ለዚህም ነው ብልጽግና ፓርቲ እንደ ፓርቲ የመንግስት የትኩረት አቅጣጫ የተጀማመሩ ሀገራዊ ፕሮጀክቶችን የመጨረስና ለህዝብና ለሀገር ጥቅም ላይ እንዲውሉ የርብርብ ማዕከል ማድረግ የተቻለው፡፡
 
እንደ ገዢ ፓርቲም ሆነ እንደ መንግስት በዋናነት ትኩረት ከተሰጣቸው ሀገራዊ ፕሮጀክቶች ውስጥ ታላቁ የህዳሴ ግድብ አንዱ ነው፡፡ ግድቡ ለኢትዮጵያዊያን ያለው ትርጉም ከፍ ያለ ነው፡፡
 
ሀይል ከማመንጨት ባሻገር የመተባበር፣የአንድነት፣እርስ በእርስ ያለንን ግንኙነት ያጠናከረ፣ ከአፍሪካ ቀንድ አገራት ጋር ያለንን ኢኮኖሚያዊ፣ፖለቲካዊና ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነታችንን የበለጠ የሚያጎለብት እንዲሁም የይቻላል መንፈስን ያሣዬን ጭምር በመሆኑ መላው ኢትዮጵያዊያን በተያዘለት ጊዜ ተጠናቆ የኤሌክትሪክ ኃይል እንዲያመነጭ ከዚህ ቀደም ያደርጉት የነበረውን ድጋፍ አጠናክረው ሊቀጥሉ ይገባል፡፡
 
መሰረታዊ የሆኑትን እና ሃይል ከማመንጨት ባሻገር ግድቡ በግንባታም ሂደት ውስጥ ሆኖ ያስገኛቸው በርካታ ትሩፋቶች አሉ፤ የመጀመሪያውና መሰረታዊው ነገር እንደ ሀገር ብሄራዊ መግባባትን የፈጠረ ግድብ መሆኑ ነው።
 
የግድቡ ግንባታ የመሰረት ድንጋይ ከተቀመጠበት እለት ጀምሮ የኢትዮጵያ ህዝብ ያለምንም የፖለቲካም ሆነ የሃይማኖት ልዩነት ሁሉም ከልጅ እስከ አዋቂ ያሳየው ድጋፍ፣ የሃገራችን ብሄሮች ብሄረሰቦች እና ህዝቦች ያሳዩት ተነሳሽነት እና በግድቡ ዙሪያ የፈጠሩት አንድነት ከመቼውም በላይ እነዲቀራረቡ እና በጋራ እንዲረባረቡ ማድረጉ ብሄራዊ መግባባትን በመፍጠር በየትኛውም ዘርፍ ለተያያዝናቸው አጀንዳዎች ትልቅ እና የገዘፈ ብሄራዊ አቅም ፈጥሮልናል፡፡
 
ሁለተኛው ደግሞ ህዝቡ ስለአባይ ያለውን ቁጭትና ከሃይል የዘለለ ሉአላዊነትን በተመለከቱ ጉዳዮች ላይ መንግስት የማይደራደር እንደሆነ ስለሚገነዘብ መሆኑ አያጠያይቅም። ስለሆነም የመሰረት ድንጋዩ በኖረበት ማግስት ተጨማሪ ጥሪ ለህዝቡ ሳያስፈልግ በእልህ እና በቁጭት ተነስቷል።
 
እንደ ህዝብ ለዘመናት ተጠናውቶን የነበረውን የተረጂነት እና የተመጽዋችነት መንፈስ ከጫንቃችን አሽቀንጥረን በመጣል የይቻላል መንፈስን ሰንቀን በተግባርም እንድናረጋግጥ ያስቻለን በመሆኑ ነው፡፡
 
ሶስተኛውና ሌላኛው ትሩፋቱ ደግሞ የስራ እድል ነው። በግንባታ ሂደት አስራ አንድ አመታትን ያስቆጠረው የታላቁ የኢትዮጵያ የህዳሴ ግድብ ግንባታን መጀመር ተከትሎ ሰፊ የሰው ሃብት በግድቡ ግንባታ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ መንገድ በመሰማራት የዕለት ኑሮውን እያሸነፈ ነው፡፡
 
ከከፍተኛ ባለሙያዎች ጀምሮ እስከ ጉልበት ሰራተኛ ድረስ በግንባታው ስራ በመሳተፍ ባጠቃላይ ወደ 13ሺ ለሚጠጉ ሰራተኞች ሰፊ የስራ ዕድል የፈጠረ ግዙፍ ፕሮጀክት መሆኑን የፕሮጀክቱ ኃላፊዎች ሲናገሩ ይደመጣል፡፡ ከዚሁ ጋር ተያይዞ ፕሮጀክቱ የፈጠረው አራተኛ ሊሆን የሚችለው ትሩፋት የቴክኖሎጂና የእውቀት ሽግግር ነው።በግድቡ ግንባታ ላይ የሚሰሩ ኢትዮጵያውያን ከፍተኛ የእውቀት፣ የክህሎት እና የቴክኖሎጂ ልምድ እያገኙ ነው፡፡
 
ሌላውና ዋናው የዲፕሎማሲ ድል ነው፡፡ኢትዮጵያ የግድቡን ግንባታ መጀመሯ ቀድሞውንም የእግር እሳት የሆነባትና በዚሁ ምክንያት ከአፍሪካ ርቃ የቆየችው ግብጽ ከብዙ ውጣ ውረድ በኋላ ጉዳዩን የአፍሪካ ህብረት እንዲመለከተው ስምምነት ላይ መደረሱ አለማቀፋዊ ትሩፋቱም የገዘፈ ውድ ፕሮጀክታችን እንደሆነ ማሳያ ነው፡፡
 
በመሆኑም ለዚህ ግድብ ግንባታ ያለምንም የውጭ ድጋፍም ሆነ ብድር በራሳችን አቅም ተጠናክረን ግድቡን እዚህ ደረጃ ላይ ማድረሳችን ለአፍሪካም ሆነ ዓለም ላይ ላሉ ሃገራት በራሳቸው አቅም ህዝባቸውን አስተባብረው ማደግ እንደሚችሉ ያሳየ የሰንደቅ ዓላማ ፕሮጀክታችን ነው፡፡

ምላሽ ይስጡ