ምንም እንኳ ከለውጡ ወዲህ በርካታ ቱርፋቶችን ማግኘት ብንችልም እንደ አገር መፈታት ያለባቸው ውስብስብ አያሌ የቤት ስራዎች እንዳሉብን ይታወቃል፡፡
ካለፉት ጊዚያት ጀምሮ ለውጡ የሚፈለገውን ያህል እንዳይራመድ እንቅፋት የሆኑ ፈተናዎች እንደ የበረሃ አንበጣ፣ድርቅ፣ከአሸባሪው ህወኃት ጋር የተደረገ የህልውና ጦርነት፣የዜጎች መፈናቀል፣የኮቪድ 19 ወረርሽኝ አሁን ደግሞ የኑሮ ውድነቱና የዋጋ ግሽበቱ ፈተናዎች ሆነው ቀጥለዋል፡፡
እነዚህን እና መሰል ፈተናዎችን እንደ አገር የደቀኑትን አደጋ በቅጡ ተረድተን አፋጣኝ ምላሽ መስጠት የማንችል ከሆነና በዚሁ ከቀጠለ የህልውናችን፣ የሰላማችን፣ የደህንነታችንና የጸጥታችን ስጋት ሊፈጥር እንደሚችል መገንዘብ ያሻናል፡፡
ታሪክ እንደሚያሳየው ከሆነ ዓለም ላይ ከተነሱ የአገራት አብዮቶች መካከል ቁጥራቸው የበዛው ምክንያታቸው መረጋጋት ያቃተው የኢኮኖሚ ችግር እንደሆነ ነው፤የራሽያው የጥቅምት አብዮትና ፣ የ1966ቱ የጸደይ አብዮቶች የተቀሰቀሱት በኢኮኖሚያዊ ቀውስ መሆኑን የታሪክ መዛግብት ያወሳሉ፡፡
የዋጋ ግሽበትን ተንተርሶ የሚመጣ የኢኮኖሚ መዋዠቅ በጊዜ መስመሩን እንዲይዝ ካልተደረገ ለውጡን ከማደናቀፍ አልፎ ለሰላምና መረጋጋት ዕጦት ምክንያት ሊሆነን ይችላል፡፡
ታዲያ እኔና እናንተ በዚህ ያልደነገጥን በምን ልንደነግጥ ነው? እንዲህ አይነቱን ስጋት በአንድነት ሆነን መፍትሔ ካልሻትን የጸናች ኢትዮጵያ ለማዬት አዳጋች ይሆንብናል፡፡
የኑሮ ውድነት፣ የዋጋ ግሽበት ፣ ስራ አጥነት ፣ ድህነትና ሌሎች ኢኮኖሚያዊ ችግሮች በጊዜ እንዲፈቱ ካስፈለገ መላው ኢትዮጵያዊያን ከመንግስታችን ጎን ሆነን ህገ ወጦችን መዋጋት ይኖርብናል፡፡
እነዚህ የኢኮኖሚ መሠረታዊ ጉዳዮች ጤናማ መሆን ከቻሉ ህዝብን የማረጋጋት ሃይል እንዳላቸው ሁሉ ጤናማ ካልሆኑ ሕዝብን በአሉታ ማለትም ለተቃውሞና ለአመጽ ማነሳሳታቸው አይቀርም ።በኢኮኖሚው ላይ የምናያቸው ስኬቶችም ሆነ ውድቀቶች ከፖለቲካው በላይ ጉልበት እንዳላቸው ጎረቤት አገር ሱዳንን ማንሳት በቂ ነው።
በሱዳን በዳቦ ላይ በተደረገ የ10 ሳንቲም ጭማሪና ሌሎች ተያያዝ ምክንያቶች የተነሳ ሁከትና ብጥብጥ ተነስቶ በርካቶችን ለሞት ሲዳርግ ቁጥራቸው ቀላል የማይበሉትን ደግሞ ለአካል ጉዳት መዳረጉ የቅርብ ጊዜ ትውስታችን ነው፡፡ከፖለቲካ ጉዳዮቻችንን ጎን ለጎን ለኢኮኖሚያችን ልዩ ትኩረት መስጠት የግድ ከሚለን ጊዜ ላይ ደርሰናል፡፡
ለኑሮ ውድነቱና ለዋጋ ግሽበቱ በቂ ትኩረት በመስጠት ህዝብ ለሚያነሳው እሮሮ አጥጋቢ ምላሽ መስጠት የግድ ያስፈልጋል፤ይህ ሳይሆን ቀርቶ የኑሮ ውድነቱና የዋጋ ግሽበቱ በዚህ ከቀጠለ ከአሸባሪዎቹ ህወኃትና ሸኔ በላይ የህልውናችን አደጋ፣የደህንነትና የጸጥታ ስጋት የመሆን አዝማማሚያ ሊፈጥሩ እንደሚችሉ በልኩ መረዳት ይኖርብናል፡፡
የዋጋ ግሽበትና የኑሮ ውድነት ከዳር እስከ ዳር ለመላው ኢትዮጵያዊያንን መነጋገሪያ አጀንዳ የሆነ፣የዜጎችን ኑሮ በብርቱ እየተፈታተኑ የሚገኙ በመሆናቸውና ከኢኮኖሚያዊ ችግርነት አልፈው ማህበራዊና ፖለቲካዊ ቀውስ እንዳይፈጥሩ ተገቢው ትኩረት እንደሚሰጣቸው የገዢው ብልጽግና ፓርቲ አመራሮች በቅርቡ ከህዝብ ጋር በነበራቸው ህዝባዊ ውይይት አንስተዋል፡፡
መንግስት ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት ምርትንና ምርታማነትን ለማሳደግ ኩታ ገጠም ግብርናን፤ የቆላ ስንዴን ፤ የግብርና ሜካናይዜሽንን ለማስፋፋት፤ የአረንጓዴ አሻራን ለማሳካት ከፍተኛ ጥረት እያደረገ ይገኛል።
ምርት ማሳደግ ብቻውን መፍትሔ አይሆንምና ዋናው ትኩረት ሊሰጥ የሚገባው ጉዳይ ብልሹ የግብይት ስርዓትን በአግባቡ ማረምና ተገቢውን ክትትል ማድረግ፤ የዋጋ ግሽበት እንዲፈጠር ምክንያት የሆኑ ደላሎችን ከገበያው ማስወጣት፤ በቂ ምርት እያለ ተገቢ ባልሆነ ምክንያት የዋጋ ጭማሪ ለማድረግ በየቦታው የሚከዝኑ ስግብግብ ነጋዴዎች ላይ አስተማሪ እርምጃዎችን መውሰድ፣የኢኮኖሚ አሻጥረኞችን በሕግ ስርዓት ማስያዝና በህግ ተጠያቂ ማድረግ ያስፈልጋል፡፡
ሆኖም ይሄ ሁሉ ችግር በመንግስት የተናጠል ጥረት ብቻ ሊፈታ ስለማይችል ልዩ ልዩ ሲቪክ ማህበራት፣ የንግድና የዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት፣ የኢትዮጵያ ሸማቾች ማህበራት፣የፀጥታ አካላት እና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ተቀናጅተውና ተናበው መስራት ይጠበቅባቸዋል።