መደመር የመከፋፈልን ግንብ አፍርሶ፤ ዘረኝነትና ጎጠኝነትን ያስወግዳል፡፡ መደመር አንድነት የሚነግስበት ሰው በሰውነቱ ብቻ ክብሩና ነጻነቱ ተጠብቆ እንዲኖር እድል የሚሰጥ ነው፡፡
መደመር የሚፈነጥቀው የወንድማማችነ ጮራ ትውልድ ተሻጋሪ ነው፡፡ ምክነያቱ ደግሞ መደመር ትብብር፣ መተጋገዝ፣ መደጋገፍን የሚያበረታታ በዛሬ መሰረት ነገን ማነጽ የሚያስችል እሳቤ በመሆኑ ነው፡፡
የመደመር እሳቤ ከዴሞክራሲ ስርዓት አንጻር ክፍተቶችን አርሞ የመግባባት ዴሞክራሲን በተሻለ መሰረት ላይ ለመገንባት እድል የሚሰጥ እሳቤ ነው፡፡ በአገራችን ማናቸውም መብቶች እርስ በእርስ የማይቃረኑበትና ለአገር አንድነት ፈተና የማይሆኑበትን ሁኔታ መፍጠር የሚቻለው በመደመር ውስጥ ሲተገበሩ ብቻ ነው፡፡
መደመር አብዛኞቹ የአገር ህልውናን የሚፈታተኑ ችግሮች በወንድማማችነት ማዕቀፍ ውስጥ የሚፈታ፤ ፍትሃዊነትን እና እኩልነት እንዲጎለብቱ የሚያደርግ ነው፡፡ ዶ/ር ዐቢይ አሕመድ ስለመደመር ሲያብራሩ “መደመር እሩቅ አልሞ ከትንሽ የመጀመር የሺህ ማይል ጉዞ ነው፤ የመደመር መንገዱ የዛሬን አቅም ሰብስቦ በትናንት ጥሪት ላይ በማማከል ለነገው የብልጽግና መደረሻ ወረት እያካበቱ መሄድ ነው፤ የመደመር መንገድ ከሌላ ፍጥረታት ሁሉ በሰው ልጆች ዘንድ ይሰራል፡፡” ብለዋል፡፡
በእርግጥም ነገሮችን በአስተውሎት መመልከትና ማመዛዘን የሚችለው የሰው ልጅ እኔ ብቻ ከሚል የስግብግብነት ስሜት ተላቆ በጋራ መስራትን፣ በጋራ ማደግንና አብሮ መለወጥ ተግባራዊ ማድረግ አያዳግተውም፡፡ በመሆኑም መደመር ለሰው ልጆች ሁሉ የሚሰራ እና ወደሁለንተናዊ ብልጽግና የሚያሻግር እሳቤ ነው የሚባለው፡፡ የአገራችንን እጣፈንታ ማሳመር የሚቻለው አብሮነታችንን በመኮትኮትና በሁኔታዎች የማይናጋ ማህበረሰባዊ አንድነትን በመፍጠር ብቻ ነው፡፡ ለዚህ ደግሞ መደመር ሁነኛ መላ ነው፡፡