ከቂም በቀል፣ ከጥላቻና ከደም መፋሰስ የፖለቲካ ባህል ተላቀን የሰለጠነ የፖለቲካ ዘይቤን በመትከል ለቀጣዩ ትውልድ ወንድማማችነትና መተባበርን ሰላማዊ የፖለቲካ ልምምድን ማውረስ ይኖርብናል፡፡ብዝሃነታችንን በሚያስተናግድ መልኩ ህብረ ብሄራዊ አንድነታችንን ማጠናከርና ጠንካራ ኢትዮጵያን መገንባት ላይ መረባረብ ለነገ የምንለው ስራችን አይደለም፡፡
ከሚለያዩንና ከሚበታትኑን ነገሮች ይልቅ የሚያስተሳስሩን አንድ የሚያደርጉን ነገሮች እጅግ በርካታ በመሆናቸው ከመነጣጠል ይልቅ መተባበርና ለጋራ ዓላማ በአንድነት መቆም የሚያዋጣን መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐብይ አህመድ በአንድ ወቅት መናገራቸው ይታወሳል፡፡
በዋና ዋና አገራዊ ጉዳዮች ላይ ተከታታይ የልሂቃንና ህዝባዊ ውይይቶችን ማድረግና አገራዊ መግባባት መፍጠር ከአስፈላጊነቱም በላይ ለኢትዮጵያዊያን አንድነት መጠንከር ጉልህ ሚና ይጫወታል፡፡
የብሄር፣ የሃይማኖት፣ የባህል፣የቋንቋና ሌሎች በርካታ የማንነት መገለጫዎች ባሉባት ኢትዮጵያ ብዝሃነታችንን እንደ ውበትና እንደ ጥንካሬ ምንጭ በመጠቀም ሁሉም ዜጋ ኢትዮጵያ የእኔ ናት እንዲል አሳታፊና አካታች የዴሞክራሲ ሥርዓት መገንባት እጅግ አስፈላጊ ነው፡፡