በኮቪድ ምክንያት የአፍሪካ ህብረት የመሪዎች ጉባኤ ላለፉት ሁለት ዓመታት የፊት ለፊት ስብሰባ ሳይደረግ ቆይቶ ነበር፡፡ጉባኤው በአዲስ አበባ እንዳይካሄድ ኮቪድ 19 እና በሰሜኑ የሀገራችን ክፍል መንግስት ህግ ለማስከበር በተወሰዱ ገንቢ እርምጃዎች የተከፉ አንዳንድ ወገኖች ስውር እጆች በመኖራቸው ምክንያት ጫናዎች እንደነበሩ ይታወቃል ።
እነዚህን ለመሻገር በኢትዮጵያ በኩል ከከፍተኛ የመንግስት ሀላፊዎች፣በአገር ውስጥም በውጭም በሚገኙ ዲፕሎማቶች፣ በተለያዩ እርከኖች ውስጥ የሚገኙ በውጭ ግንኙነት ዘርፍ በስራ ላይ ያሉ ወገኖች ባደረጉት ተከታታይ ዲፕሎማሲያዊ ጥረት፥ የአፍሪካ ወንድሞቻችንና እህቶቻችን በአሁኑ ሰዓት የኢትዮጵያን ነባራዊ ሁኔታ በሚገባ በመረዳት፣ ለኢትዮጵያውያንም ወገንተኝነትን ለመግለጽ እንዲሁም ከኢትዮጵያ ህዝብ ጋር ለመቆም ባላቸው ፍላጎትና ስሜት አዲስ አበባ በአካል እንዲደረግ ውሳኔ ላይ መድረስ ተችሏል፤ይህ ደግሞ የአገራችንን ነባራዊ ሁኔታ እንዲረዱት የሚያስችል ትልቅ ድል ነው።
ብዙ የአፍሪካ ሀገራት መሪዎች ኢትዮጵያ ለአፍሪካ ነጻነት ፣ ሉዓላዊነትና ሰላም የምታደርገውና ስታደርግ የኖረችውን ተጋድሎ በሚገባ ስለሚረዱ ከኢትዮጵያ ጎን መሆናቸውን ለማሳየት ጉባኤው በአካል በአዲስ አበባ እንዲሆን መወሰን መቻላቸው በርግጥም የኢትዮጵያን ውለታ በአግባቡ መረዳታቸውን የሚያሳይ ነው።
ምንም እንኳን ስውር እጆች ይህንን ለማስቆም ያደረጉት ጥረት ቢኖርም የሚሰማ ጆሮ ባለመኖሩ እነዛን ለተቃውሞ የተዘረጉ እጆች በአፍሪካውያን ሃያል ድምጽ ቦታ እንዲያጡ ተደርገዋል፡፡ ይህም አጋጣሚ የኢትዮጵያን ገጽታ ሲያጠለሹ የነበሩ ሀይሎች አንገታቸው የደፉበትና ያፈሩበት ሆኗል፡፡
ኢትዮጵያዊያን ፈተናዎቹን ሁሉ አልፈን ጉባኤውን እንድናስተናግድ ዕድል ማግኘታችን መዲናችን አዲስ አበባ ፍጹም የተረጋጋች፣ ዲፕሎማሲያዊ እንቅስቃሴ እና ሌሎችም እንቅስቃሴዎች የሚካሄዱባት መዲና መሆኗን እንግዶች በተግባር እንዲያዩት ዕድል ይፈጥርላቸዋል፡፡
መንግስት ጉባኤውን በተሳካ ሁኔታ ለማስተናገድ ብሄራዊ ኮሚቴ አቋቁሞ ከፍተኛ ዝግጅት አድርጎ ወደ ተግባር መግባቱ ይታወቃል፡፡ጉባዔው የተሳካ እንዲሆን ሁሉም ዜጋ በኢትዮጵያዊ ጨዋነትና ኃላፊነት እንግዶቻችንን ተቀብለን በአግባቡ ማስተናገድና ጉባኤውን ሲጨርሱም ወደየአገራችሁ በሰላም ግቡ ብለን መርቀን መሸኘት ይኖርብናል፡፡ ምክንያቱም በዚህ አስቸጋሪ ጊዜ አፍሪካውያን ወንድሞቻችን እኛን ብለው ከያሉበት ተጠራርተው ስለሚመጡ በአፍሪካዊ ስሜት ማስተናገድ ውዴታ ብቻ ሳይሆን ግዴታችንም ሊሆን ይገባዋል።የአፍሪካ ህብረት የመሪዎች ጉባኤ ጥር 28 /2014 እና ጥር 29/2014 ዓ.ም በአዲስ አበባ ይካሄዳል፤