ተገደን ለገባንበት ጦርነት ጥሩ ደጀን እንዳለን አይተናል፡-ክብርት ፕሬዝደንት ሳህለወርቅ ዘውዴ
በድሬዳዋ እየተካሄደ በሚገኘው የ16ኛው የብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች በዓል ሲምፖዚየም ላይ በክብር እንግድነት የተገኙት የኢፌዴሪ ፕሬዝደንት ክብርት ሳህለ ወርቅ ዘውዴ ዛሬ እየተከበረ ያለው ይህ በዓል ካለፉት ዓመታት በእጅጉ የተለዬ መሆኑን ጠቅሰው የአገራችን ህልውና በከፍተኛ ደረጃ ፈተና ላይ በወደቀበት ወቅት መከበሩና የአገራችን ዋና ምሰሶ የሆነው የአገር መከላከያ ሰራዊታችን የተጠቃበትና 13 ወራት ያስቆጠረ የእርስ በእርስ ጦርነት በተካሄደበት ወቅት ላይ መከበሩ ልዩ ያደርገዋል ብለዋል፡፡
የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባኤ የተከበሩ አቶ አገኘሁ ተሻገር በበኩላቸው በአገር አቀፍ ደረጃ እየተከበረ በሚገኘው ይህ በዓል ህብረ ብሔራዊነትን ለማክበር ብዝሃነትን አምኖ መቀበል ይገባል ያሉ ሲሆን ብዝሃነታችን ለልዩነታችን ሳይሆን ለወንድማማችነታችን፣ለፍቅር እንጂ ለጸብ መነሻ እንዳይሆን ጥንቃቄ ማድረግ ይኖርብናል ብለዋል፡፡
ሁሉም ነገር የሚያምረው ኢትዮጵያችን ሉዓላዊነቷ ተከብሮ እስከኖረች ብቻ ነው ያሉት አፈ ጉባኤው ሁላችንም አንድነታችንን ጠብቀን፣ሉዓላዊነታችንን አስከብረንና በኢትዮጵያችን ህልውና ሳንደራደር የጋራ ጥቅማችንን ለማረጋገጥ ከጫፍ ጫፍ እስከተነሳን ድረስ የሚያቆመን አንዳች ኃይል የለም ሲሉ ተናግረዋል፡፡
በሲምፖዚየሙ ላይ ጥናታዊ ጽሁፋቸውን ያቀረቡት በፌዴሬሽን ምክር ቤት የህግ ጉዳዮች አማካሪ የሆኑት ዶ/ር ዘለቀ የኢትዮጵያ ብሔሮች ብሔረሰቦችና ሕዝቦች የተዛመዱና የተጋመዱ እርስ በእርስም የተወራረሱ መሆናቸውን ጠቅሰው የሀገሪቱን ፌዴራላዊ ሥርዓት ስሙን ብቻ ሳይሆን አተገባበሩም በትክክል ሲፈጸም ያየንበት ወቅት ላይ ደርሰናል ብለዋል፡፡
በሲምፖዚየሙ ላይ ከመላው ሀገሪቱ የተውጣጡ የኢትዮጵያ ብሔር፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች የተሳተፉ ሲሆን የየብሄሩ ልዑካን አባላት የየአካባቢያቸውን ጭፈራ፣ አለባበስ፣ የተለያዩ ቁሶች እና ሌሎች መገለጫዎቻቸውን አሳይተዋል፡፡