ወንድማማችነት ለህብረ ብሔራዊ አንድነት በሚል መሪ ቃል 16ኛው የብሔር፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች በዓል እየተከበረ ነው
ወንድማማችነት ለህብረ ብሔራዊ አንድነት በሚል መሪ ቃል 16ኛው የብሔር፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች በዓል ዋዜማ በድሬዳዋ ከተማ በድምቀት እየተከበረ ይገኛል፡፡
በዋዜማ በዓል ላይ ተገኝተው ንግግር ያደረጉት የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈጉባኤ ክቡር አቶ አገኘሁ ተሻገር የበዓሉ መከበር ዋና ዓላማ የኢትዮጵያ ብሔር፣ብሔረሰቦችና ህዝቦች የእርስ በእርስ ትስስርን በማጠናከር በብዝሃነት ላይ የተመሰረተ ህብረ ብሔራዊ አንድነት በማጎልበት ለጋራ አገራዊ ጥቅም ዓላማ በጋራ መቆም ማስቻል ነው ብለዋል፡፡
አፈ ጉባኤው አያይዘውም ይህ በዓል ካለፉት ጊዚያት የሚለየው አሸባሪው የህወኃት ቡድን በአገራችን ላይ ህገ መንግስቱንና ህገ መንግስታዊ ስርዓቱን በሃይል ለመናድ ያጣውን ስልጣን በጉልበት ለመያዝ ከኢትዮጵያ ታሪካዊ ጠላቶች ጋር በማሴር የከፈተብንን ፖለቲካዊ፣ኢኮኖሚያዊ፣ዲፕሎማሲያዊና የሚዲያ ጦርነት ለመመከትና ለመቀልበስ ከምንጊዜም በላይ በተጠናከረ አንድነት በምንፋለምበት ጊዜ መከበሩ ነው ሲሉ ተናግረዋል፡፡
የድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ክቡር አቶ ከድር ጁሃር በበኩላቸው አሁን የምንገኝበት ምዕራፍ እንደ ሀገር በአንድ በኩል በሀገራችን ታይቶ በማይታወቅ መልኩ ወደ ለውጥ ምዕራፍ የገባችበትና በዚህም ተስፋ ሰጪ ውጤቶች እየተመዘገቡ መሆኑን የጠቀሱት ከንቲባው በሌላ በኩል ለሀገርና ለወገን ቅድሚያ በመስጠትና ውጤታማ በመሆን ሀገርንና ትውልድን ለማሻገር የሞት ሽረት ትግል ላይ የምንገኝበት ወቅት ነው ብለዋል፡፡
በመጨረሻም ከመላው አገሪቱ የተወጣጡ የብሔር፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ተወካዮች በታደሙበት ልዩ አገራዊ የሙዚቃ እና የእራት ስነ ስርዓት ላይ የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ክቡር አቶ አገኘሁ ተሻገርን ጨምሮ በርከታ የፌደራል ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች፣ የክልል ርዕሳነ መስተዳድሮች፣የሐይማኖት አባቶችና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል፡፡
ወንድማማችነት ለህብረ ብሔራዊ አንድነት በሚል መሪ ቃል 16ኛውን የኢትዮጵያ ብሔሮች ብሔረሰቦችና ህዝቦች በዓል ነገ በተለያዩ ዝግጅቶች በድሬደዋ አስተናግጅነት በድምቀት ይከበራል።