የብልጽግና ፓርቲና የራሽያ ዩናይትድ ፓርቲ ግንኙነታቸው በሚጠናከርበት ዙሪያ መከሩ::
የብልጽግና ፓርቲ ዋና ጽህፈት ቤት ሃላፊ አቶ አደም ፋራህ እና በኢትዮጵያ የራሽያ ፌዴሬሽን አምባሳደር የተከበሩ ሚስተር ኢቨጌኒ ቴረኺን በተደረገ ውይይት የብልጽግና ፓርቲንና የራሽያ ዩናይትድ ፓርቲን ግንኙነት በሚጠናከርበት ዙሪያ ተወያይተዋል፡፡
ከዚህ ቀደም በፓርቲዎቹ መካከል የተፈረመውን የመግባቢያ ሰነድን መሰረት ባደረገ መልኩ የፓርቲ ለፓርቲ ግንኙነቱን ተግባራዊ ለማድረግ በሚያስችሉ ጉዳዮች ዙሪያ ውይይቶችን አድርገዋል፡፡
ፓርቲዎች በኢትዮጵያ እና በራሽያ ፌዴሬሽን መካከል ያለውን ሁለንተናዊ ግንኙነት በሚያጠናክር መልኩም ለመስራት ተግባብተዋል፡፡ አቶ አደም ፋራህ በውይይቱ እንዳነሱት የኢትዮጵያና የራሽያ ፊዴሬሽን ከመቶ ዓመት በላይ ያሰቆጠረ ግንኙነት እንዳላቸው አውስተው፣ የራሽያ ፌዴሬሽን ምንግዜም ለኢትዮጵያ ለሚያደርገው ድጋፍ ምስጋና አቅርበዋል፡፡
የራሽያው አምባሳደር በበኩላቸው ኢትዮጵያና ራሽያ በተለያዩ መስክ የጀመሩትን ግንኙነት ይበልጥ ለማጠናከር የፓርቲ ለፓርቲ ግንኙነቱ ትልቅ አቅም እንደሚፈጥር አንስተዋል፡፡ በመጨረሻም አምባሳደሩ ከሞስኮ የተላከ መልዕክት ለብልጽግና ዋና ጽህፈት ሃላፊው አስተላልፈዋል፡፡