You are currently viewing ኢትዮጵያውያን በአዲስ ምዕራፍ. . . /በሚራክል እውነቱ/

ኢትዮጵያውያን በአዲስ ምዕራፍ. . . /በሚራክል እውነቱ/

  • Post comments:0 Comments
ኢትዮጵያውያን በአዲስ ምዕራፍ. . .
/በሚራክል እውነቱ/
 
ኢትዮጵያውያን በአዲስ ምዕራፍ ላይ ይገኛሉ።በየዘመኑ የተፈጠሩ አገር ወዳድ ጀግኖች ያስረከቧቸውን ክብሯና ነጻነቷ የተጠበቀ ሀገር ዛሬም ሳትደፈር እንድትቀጥል ከምስራቅ እስከ ምዕራብ፤ከሰሜን እስከ ደቡብ የሚገኙ ኢትዮጵያዊያን እጅ ለእጅ ተያይዘው ሀገራቸውን ከውስጥ ባንዳዎች እና ከውጭ ወራሪ ሀይል ሊታደጓት ዛሬም እንደትናንቱ በተጠንቀቅ ቆመዋል፡፡
 
በተለይም በትውልዶች የመስዋዕትነት ታሪክ ነጻነቷና ክብሯ እንደተጠበቀ ሉዓላዊ ሆና ለኖረችው ኢትዮጵያ ከታሪካዊ ጠላቶቻችን ጋር በመሆን የህልውና ስጋት የሆነውን አሸባሪውን ህወኃት ግብአተ መሬት ለመፈጸም እና ዘላቂ ሀገራዊ እፎይታ ለመፍጠር ዜጎች በአራቱም አቅጣጫ ለሀገር የክብር ሞት ለመሞት ዛሬም ወደ ግንባር በመትመም ላይ ይገኛሉ።
 
ቡድኑ ከአርባ አምስት ዓመታት በላይ በኢትዮጵያና ኢትዮጵያውያን ላይ የፈጸመው ግፍ፣ እንደ አገር የተፈጠረው ሀገራዊ ለውጥ ራስ ምታት ቢሆንበት መቀሌ ሄዶ በመመሸግ በተላላኪዎቹ አማካኝነት በመላ ሀገሪቱ ህጻን፣ ነፍሰ ጡር ሴት፣ ሽማግሌ፣የሐይማኖት አባት ሳይል ንጹሃን ዜጎችን በአሰቃቂ ሁኔታ ያስጨፈጨፈበት እውነታ ፣ በሀገሪቱ የቁርጥ ቀን ባለውለታ በሰሜን እዝ ላይ የፈጸመው ልብ ሰባሪ ክህደት ኢትዮጵያዊያን መቼም አይረሱትም።
 
በማይካድራ በንጹኃን ዜጎች ላይ የፈጸመው የጅምላ የዘር ጭፍጨፋ አልበቃህ ብሎት፤ በአጋምሳ፣ በጭናና በቆቦ በርካታ ንጹኃን ዜጎችን በአሰቃቂ ሁኔታ ገድሏል። በአፋር ክልል በጋሊ ኮማ በመጠለያ የሚገኙ ከአንድ መቶ በላይ ህጻናትን ጨምሮ ከሁለት መቶ ሃምሳ በላይ ንጹኃን ዜጎችን በከባድ መሳሪያ ጨፍጭፏል።
 
በዚህ አሸባሪ ቡድን እየተፈጸመ ያለው ጥቃት የውጭ ወራሪ እንኳ ይፈጽመዋል ተብሎ የሚገመት አልነበረም። እናቶች የወላድ ወግ ተከልክለው በጫካ እንዲወልዱ ግድ ሆኖባቸዋል። ህጻናት አዛውንቶችና እናቶች ከጥቃቱ ለማምለጥ ብዙ ተፈትነዋል። ልጃገረዶችና እናቶች በአሸባሪ ቡድኑ ጀሌዎች እናታቸው አባታቸው ፊት ተደፍረዋል።ምዕመናን ለፈጣሪያቸው ምስጋናና ፀሎት የሚያደርሱባቸው እነዚያ የተቀደሱ የአምልኮ ስፍራዎች በአሸባሪው የህወኃት ቡድን የጭካኔ ተግባር እንዲፈራርሱ ሆነዋል፤ፈጣሪን ሳይፈሩ ተጸዳድተውባቸዋል።
 
አርሶ አደሩ እንደ አይን ብሌኑ የሚቆጥሯቸውን ከብቶች፣ግመሎች፣በጎች፣ፍየሎች የቡድኑ አባላት እያረዱ በልተዋቸዋል፤ የዘረፏቸው፣ በጥይት ደብድበው የገደሏቸው እንስሳት ብዛትም አያሌ ናቸው። በከፍተኛ ወጪ የተገነቡ ትምህርት ቤቶች፣ የጤና ተቋማትና ሌሎች የመንግስት ተቋማት ተዘርፈው ወደ ትግራይ ተጭነዋል፤ የተቀረው ንብረታቸው ሰነዳቸው እንዲወድም ተደርጓል።
 
ይህን አረመኔያዊ ድርጊት በአደባባይ በጠራራ ጸሀይ እየፈጸመ የሚገኘው ይህ አሸባሪ ቡድን ፣ ከምዕራባውያኑ እና ከታሪካዊ ጠላቶችችን በሚያገኘው ድጋፍና በሚደረግለት ጥብቅና ከድርጊቱ ከመቆጠብ ይልቅ በድርጊቱ ገፍቶበታል።
 
ህዝባችን ይህንን አሸባሪ ቡድን ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ አስወግዶ ፊቱን ወደ ልማትና ከልማት ወደሚገኝ ከፍታ ለማዞር የደረሰበት ውሳኔ ብቸኛው የችግሩ መፍቻ ቁልፍ እንደሆነ ይታመናል።
 
ከፍጥረቱ ጀምሮ ሊገራ በማይችል የተበላሸ አስተሳሰብ ሀገርና ህዝብን ዋጋ ሲያስከፍል ለቆየው ቡድን ብዙ እድል ተሰጥቶታል፤ ከዚህ በላይ ሌላ እድል መስጠት የተበላሸ አስተሳሰቡን የመቀበልና የማበረታታት ያህል ይቆጠራልና ቡድኑን ለአንዴም ለመጨረሻ ጊዜ በማስወገድ ወደ አዲስ ምዕራፍ የምናደርገውን ጉዞ ማጠናከር ይኖርብናል፡፡

ምላሽ ይስጡ