‹‹ከአሸባሪው ህወሓት ጋር እየተደረገ ያለው ጦርነት የሁሉም ኢትዮጵያውያን ጦርነት ነው›› -አቶ ጥላሁን ከበደ የደቡብ ክልል ብልጽግና ጽህፈት ቤት ኃላፊ
አሸባሪው ህወሓት የከፈተው ጦርነት ኢትዮጵያን ማፍረስ ላይ ያነጣጠረ በመሆኑ ሁሉንም ኢትዮጵያዊ የሚመለከት የህልውና ጦርነት መሆኑን የደቡብ ብሄር ብረሰቦችና ህዝቦች ክልል የብልጽግና ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ጥላሁን ከበደ ገለጹ።
አቶ ጥላሁን ከበደ በተለይ ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንደገለጹት፣ አሸባሪ ቡድኑ ኢትዮጵያን ማዳከም ብሎም ማፈራረስ ላይ ያተኮረ ጥቃት በመሰንዘሩ ሁሉም ኢትዮጵያውያን የተከፈተብንን ጦርነት ለማክሸፍ ሊቀላቀል ይገባል።
እንደ አቶ ጥላሁን ከበደ ማብራሪያ፤ የደቡብ ብሄር ብሄረሰቦችና ህዝቦች ክልል ህዝብ አሸባሪውን ድርጅት አጥፍተን ወደ ልማት መመለስ አለብን የሚል አቋም ላይ ነው። የውጭ ኃይሎችን ደካማና እነሱ የሚሉትን ተቀብሎ የሚፈጽም መንግሥት ለመመስረትና በዚህ ሂደት ማዕቀብ ጭምር ለመጣል የአሜሪካ መንግሥት እያደረገ ያለው እንቅስቃሴ ህዝብ ያስቆጣ ሆኗል። እንደ ሀገር የውስጥ አንድነትን በማጠናከር እና ከመንግሥት ጎን በመቆም ኢትዮጵያን ማዳን አለብን ብሎ ህዝቡ ተነስቷል ብለዋል።
አሸባሪው ህወሓት የኢትዮጵያ ፖለቲካ ነቀርሳ በመሆኑ ለአንድ ወይም ለተወሰነ አካል የሚተው አይደለም ያሉት አቶ ጥላሁን ከበደ ኢትዮጵያውያን በሙሉ አንድ ሆነን ይህንን ባንዳ ለማጥፋትና ግብዓተ መሬቱን ለመፈጸም የህልውና ዘመቻው አካል መሆን አለብን ብለዋል።