ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን የተባበሩት መንግስታት ድርጅት 76ኛው ጠቅላላ ጉባኤ ላይ ካደረጉት ንግግር ዋና ዋና ነጥቦች:-
** የሰው ልጆች እውነተኛ ክብር እና ነፃነት መሰረቱ በዘላቂነት ራሳቸውን መምራት መቻላቸው ነው፤
** የከፋ ድህነት እና የእርዳታ ጥገኝነት ለፖለቲካ፣ ለአስተዳደር፣ ለደህንነት እና ለሰብአዊ ልማት ቀውሶች አባባሽ ምክንያቶች ናቸው፤
** ሀገራችን ኢትዮጵያ ለባለብዙ ወገን ተቋማት ያላሳለሰ ድጋፍ ስትሰጥ መቆየቷ የሚታወቅ ሲሆን ይህ ጽኑ አቋማችን የሚመነጨው ከይስሙላ መነሻ ሳይሆን ታሪክ እንደሚመሰክረው ሕግን መሠረት ያደረገ ሥርዓት በችግር ውስጥ በወደቀበት ወቅት ከደረሰብን በደል በመነሳት ነው፤
** አገራት ወደባለብዙ ወገን ግንኙነት መድረኮች ለመመለስ የሰጧቸውን የቁርጠኝነት ቃሎችን እናደንቃለን፤
** በዚህ ረገድ፣ የአገራት ሉዓላዊነትና እኩልነትን፣ በውስጥ ጉዳዮች ጣልቃ አለመግባትን፣ እንዲሁም በጋራ ጥቅምና መከባበር ላይ የተመሠረተ ትብብር መርሆዎች አስፈላጊነትን ደግመን ማስታወስ እንፈልጋለን፤
** ከሦስት ዓመት በፊት ኢትዮጵያ ተስፋ ሰጪ የለውጥ ጉዞ መጀመሯ የሚታወቅ ሲሆን እነዚህ የለውጥ ስራዎቻችን ለዲሞክራሲ፣ ለሰብዓዊ መብቶች፣ ለሰብአዊ ልማት እና ቀጠናዊ መረጋጋት አዲስ የተስፋ ጎህ ቀደዋል፤ ይሁንና ለውጡ ከፈተናዎች የፀዳ ነው ለማለት አያስደፍርም፡፡
** እንደማንኛውም ዴሞክራሲ፣ የዴሞክራሲ ስርዓታችን ግንባታ በመረጋጋት እና በሁከት መካከል ሚዛን ለማስጠበቅ የሚደረግ ሂደት በመሆኑ በእኛ የለውጥ ጥረቶች ውስጥ እኩልነትን እንደ መገፋት የሚቆጥሩ ቡድኖች ሚዛኑን ለማደናቀፍ እና ሁከት ለመፍጠር እንዲሁም የስርዐተ-አልበኝነትን ዕድሜ ለማራዘም የተቻላቸውን ሁሉ ጥረት ማድረጋቸውን ቀጥለዋል፤
** በእነዚህ የጥፋት መሪዎች ተዋናይነት በንጹሃን ዜጎች ላይ ሊገመት የማይቻል ኢሰብአዊ ጥቃት፣ የሁከት ማነሳሳት እና ንብረት ውድመት የደረሰ ሲሆን በመጨረሻም በኢትዮጵያ ሀገር መከላከያ ሰራዊት ላይ ጥቃት ተፈጽሟል፤
** ባሳለፍነው ዓመት ጥቅምት 24 ምሽት ምንም አይነት ጥርጣሬ ያልገባቸው የኢትዮጵያ የሀገር መከላከያ ሰራዊት አባላት ከውስጥ ጥቃት የተፈጸመባቸው ሲሆን ይህን እንደ ሀገር የገጠመንን አደጋ ለመከላከል የኢትዮጵያ መንግስት አስፈላጊውን እርምጃ ለመውሰድ ተገዷል፤
** እኛ ይህን የሰብዓዊ ድጋፍ ፍላጎት ለማሟላት እየተረባረብን ባለንበት ወቅት፣ የጥፋት ቡድኑ የተዘጋጀበትን ሰብዓዊ ቀውስ የመፍጠር እቅድ ተግባራዊ ከማድረጉ በላይ ክፋት የተሞላበት የፕሮፓጋንዳ ዘመቻ ተከፍቶብናል፤
** በግል ፍላጎቶች እና ጥቅሞች የሚዘወር ፖለቲካ እና የውጭ ፖሊሲ ዕውነታውን በመሸፈን የተዛባ የፖሊሲ ውሳኔ ሊያሰጥ እንደሚችልም ተገንዝበናል፤
** አሁን በደረስንበት ምዕራፍ የሰብአዊ አገልግሎት ድጋፍ የፖለቲካ ዓላማን ማስፈፀሚያ መሳሪያ እንደሆነ እየተገነዘብን መጥተናል፤
** ወንጀል ጠንሳሾቹና እና ደጋፊዎቻቸው የሃሰት መረጃዎችን በማቀነባበር እንዲሁም ሀሰተኛ ዘግናኝ ምስሎችን በመፈብረክ የተዛባ ግንዛቤ እንዲፈጠር ተንቀሳቅሰዋል፤
** የህዝባችን እውነተኛ ሰቆቃ በቂ እንዳልሆነ፣ የተወሰነውን የህዝብ ክፍል እንደ አረመኔ ከሚፈርጅ አስተሳሰብ ጋር ለማዛመድ ጥረት የተደረገባቸው ሃሰተኛ ውንጀላዎች ቀርበዋል፤
** የኢትዮጵያ መንግሥት የሰብዓዊ ዕርዳታ የመስጠት ግዴታውን መወጣቱ፣ የተናጠል ሰብዓዊ የተኩስ አቁም ማወጁ፣ የምርመራ ሥራዎችን እና ተጠያቂነት የማስፈን እርምጃዎችን መውሰዱ የሐሰት ውንጀላዎችን መቀልበስ አልተቻለም፤
** በዚህ ሰዓት አጀንዳ በሚቀረፅላቸው እና ቀለብ በሚሰፈርላቸው ሚዲያዎች ተከሰን፣ መርህ አልባ በሆነ ፖለቲካ ተፈርዶብን እንዲሁም በተናጠል የተጣለ ማዕቀብ ተደቅኖብን እንገኛለን፤
** በቀደሙት ጊዜያት ማእቀቦች በሌሎች ላይ ሲፈፀም መቃወማችን የሚታወስ ሲሆን በተመሳሳይ በኢትዮጵያም ላይ የሚደረግ ፍትህ እና ርቱዕ የሚጎድለው አካሄድ ተግባራዊ እንዳይሆን እንመክራለን፤ ምክንያቱም ጫና የሚያሳድሩ ማንኛውም እርምጃዎች ግንኙነቶችን አሻሽለው አያውቁም፤
** እኛ የምንወስዳቸው ጥንቃቄ የተሞላባቸው እርምጃዎች ከገጠመን የህልውና ፈተና ጋር ተመጣጣኝ ናቸ፤
** ምንም እንኳን አላስፈላጊ ጫናዎች ቢኖሩብንም፣ የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት፣ የግዛት አንድነት እና የፖለቲካ ነፃነት የማስጠበቅን ከባድ ግዴታ እንወጣለን፤
** ከወዳጆቻችን የሚቀርብልን ትብብር እና ቅን አሳቢነት ተቀባይነት ቢኖረውም ገንቢ አቀራረብን የመጠቀም፣ መተማመንን የማዳበር እና መረዳትን የመፍጠርን አስፈላጊነት እናሳያለን፤
** በአንድ ግዛት ውስጣዊ ጉዳይ ላይ ድጋፍን ወይም አልፎ ተርፎም አስተያዬት ለማውጣት የሚደረግ ሙከራ ስለችግሩ ውስብስብነት ሙሉ ግንዛቤን ይጠይቃል፤
** ሊታወቅ የሚገባው፤ እያጋጠመን ያለው ፈተና በኢትዮጵያ ድንበሮች ላይ ብቻ የተወሰነ አይደለም፤ መላው የአፍሪካ ቀንድ በዚህ ቡድን የተነደፈለትን አጥፊ መንገድ እየተጋፈጠ ነው፤
** ከዚህ ወንጀለኛ ቡድን ጋር የሚደረገውን ግብግብ ኢትዮጵያ እንድታሸንፍ መደገፍ የአካባቢያዊ ሰላምን ለማስቀጠል ይረዳል፤
** ውይይት ሁል ጊዜ የእኛ ተመራጭ የድርጊት አካሄድ ነው፤ በዚህ መሠረት ኢትዮጵያ ለሰላም እልህ አስጨራሽ እንቅስቃሴዎች ክፍት ናት፤ ከዚህ ጋር በተያያዘ ከአፍሪካ ህብረት እና ከአፍሪካ ቀንድ ከፍተኛ ተወካይ ጋር ኢትዮጵያ መር ብሔራዊ ውይይት ለመምራት እንሰራለን።
** ኢትዮጵያ ለማንም የደህንነት ስጋት ሆና አታውቅም። ኢትዮጵያ በህዝቦቿ ጽኑ አቋም ሁሌም ሰላም ወዳድ ሀገር ሆና የምትኖርና ቀጠናዊ እና ዓለም አቀፋዊ ሰላም ወደነበረበት እንዲመለስ የበኩሏን አስተዋፅኦ የምታበረክት ትሆናለች፤
** ኢትዮጵያ ሌሎች በተቋሞቻቸው ላይ የደረሱባቸውን ጥቃቶች ሲታደጉ ላበረከተችው ድጋፍና ትብብር ተመሳሳይ ድጋፍ ትሻለች፤ ትጠይቃለችም፡፡