የማያግባቡ በርካታ ጉዳዮች ቢኖሩም በአገር ጉዳይ ላይ ግን አንድ መሆን ይኖርብናል፡-አቶ ተስፋዬ ቤልጂጌ
በወቅታዊ አገራዊ ጉዳዮች ዙሪያ በአዲስ አበባ ከሚኖሩ የትግራይ ክልል ተወላጆች ጋር በስካይ ላይት ሆቴል ውይይት እየተካሄደ ይገኛል፡፡
ስብስባውን የመሩት በብልጽግና ፓርቲ ዋና ጽ/ቤት የፖለቲካና ርዕዮተ ዓለም ግንባታ ዘርፍ ኃላፊ የሆኑት አቶ ተስፋዬ ቤልጂጌ ኢትዮጵያዊያን ልዩነቶቻችንን አስወግደን እንደ አገር የሚገጥሙንን ችግሮች ለመፍታት በአንድ መቆማችን ትናንትም የነበረ ዛሬም ያለ፤ ነገም የሚኖር ነው ያሉ ሲሆን ከውስጥም ከውጭም የሚገጥሙንን ፈተናዎች ለመፍታት ከምንጊዜውም በላይ አንድነታችንን ልናጠናክር ይገባል ብለዋል፡፡
በስብሰባው የታደሙት የትግራይ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ትዴፓ) ሊቀ-መንበር ዶክተር አረጋዊ በርሄ በበኩላቸው የአሸባሪው የህወኃት ቡድን ዓላማ ህዝቡን ጦርነት ውስጥ በመማገድ እና ተመልሶ ስልጣን ላይ በመውጣት አገሪቱን ለምዕራባዊያን ባርነት ለማስገዛት ብሎም ጨቋኝ እና ከፋፋይ ስርዓት እንዲፈጠር ማድረግ ነው ሲሉ ተናግረዋል፡፡
ዶ/ር አረጋዊ አያይዘውም ኢትዮጵያ እና ህዝቦቿ ሰላም ውለው እንዲያድሩ ካስፈለገ ለውጡን ለማደናቀፍ የሚጥረውን አሸባሪው የህወኃት ቡድንን እስከ መጨረሻው ታግሎ ማስወገድ ነው ለዚህም መላው የትግራይ ተወላጅ ማህበረሰብ ከመንግስት ጎን ሊቆም ይገባል ብለዋል፡፡
ሌላኛው የመድረኩ ተሳታፊ አቶ ምዑዝ ገብረ ህይወት በበኩላቸው አሸባሪው የህወኃት ቡድን አገሪቱን ለመበታተን እያደረገ ያለውን ጥረት እኛ የትግራይ ተወላጆች እናወግዘዋለን ያሉ ሲሆን የትግራይ ህጻናትን ሻይ ውስጥ ሃሸሽ በመጨመር እና ጦርነት ውስጥ እንዲገቡ በማድረግ በዓለም አቀፍ ደረጃ የተቀመጡ ድንጋጌዎች ጥሷል ሲሉ ተናግረዋል፡፡
ሰራዊታችን በግንባር እየፈጸመ ያለውን ድል በዲፕሎማሲ ስራችንም ሊደገም ይገባዋል ያሉት ደግሞ ታጋይ መሰሉ ሲሆኑ ለውጡን የሚደግፉና የማይደግፉ የትግራይ ተወጆች መለዬት መቻል አለበት ያሉ ሲሆን መላው ትግራዋይ በአንድ ልንደራጅና ኢትዮጵያዊነታችንን ልናቀነቅን ይገባል ሲሉ ተናግረዋል፡፡
አሸባሪውን የህወኃት ቡድን ለመፋለም ግንባር ድረስ ለመዝመት ዝግጁ ነን ያሉት ደግሞ ኮሎኔል ፍስሃ ገብረ መድህን ሲሆኑ ከመንግስት ጎን ተሰልፈን ይህን አሸባሪ ቡድ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ማስወገድ ያስፈልጋል ብለዋል፡፡