የብልጽግና ፓርቲ ጽ/ቤት ሠራተኞች ለመከላከያ ሰራዊት የደም ልገሳ አደረጉ
(አዲስ አበባ፣ ነሃሴ 5፣ 2013 ብልጽግና ፓርቲ ጽ/ቤት) በብልጽግና ፓርቲ ዋና ጽ/ቤት የሚገኙ አመራሮችና ሰራተኞች የደም ልገሳ በማካሄድ ለመከላከያ ሰራዊት ያላቸውን አጋርነት በተግባር አሳይተዋል፡፡
የጽ/ቤቱ ሰራተኞች ከዚህ ቀደም ደጀን ለሆነው የመከላከያ ሰራዊት ገንዘባችንን አንሰስትም በሚል የአንድ ወር ደመወዛቸውን ለመከላከያ ሰራዊት ድጋፍ ያደረጉ ሲሆን በዛሬው ዕለትም በግንባር ህይወቱን ሳይሰስት እየሰጠ ለሚገኘው የመከላከያ ሰራዊት የደም ልገሳ አካሂደዋል፡፡
ሀገርን ከጠላት ለመከላከል በሚደረግ ጥሪ ላይ መሳተፍ ከእያንዳንዳችን ይጠበቃል ያሉት አስተያየት ሰጪዎቹ በገንዘብ የማይተመነውን ደም ለሀገር መከላከያ ሰራዊት በመለገሳቸው ብሎም ደመወዛቸውን ጭምር በመስጠታቸው መደሰታቸውን ገልጸዋል፡፡
በመጨረሻም የጽ/ቤቱ ሰራተኞችና አመራሮች የህግ ማስከበር ዘመቻው እስኪጠናቀቅ ድረስ የሚያደርጉትን ድጋፉ አጠናክረው እንደሚቀጥሉና ከገንዘብ ድጋፍና ደም ከመለገስ ባሻገር ግንባር ድረስ ሄደው ግዳጃቸውን ለመወጣት ዝግጁ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡