‹‹ አንዳንድ የውጭ ኃይሎች በኢትዮጵያ ላይ ዘመቻ የከፈቱት መንግሥት ለነሱ ጥቅም ባለመቆሙ ነው ››
– የህግ መምህርና የማህበረሰብ አንቂ ሙክታር ኡስማን
አንዳንድ የውጭ ኃይሎች በኢትዮጵያ ላይ ዘመቻ የከፈቱት አሁን ኢትዮጵያን እየመራ ያለው መንግሥት አሸባሪው ህወሓት ስልጣን ላይ እያለ እንደነበረው ለነሱ ጥቅም የቆመ ባለመሆኑ እንደሆነ የህግ መምህርና የማህበረሰብ አንቂው አቶ ሙክታር ኡስማን አስታወቁ።
አቶ ሙክታር ለአዲስ ዘመን እንደገለጹት፤ አሁን ስልጣን ላይ ያለው የኢትዮጵያ መንግሥት በራሱ የሚተማመንና እንደ አሸባሪው ህወሓት ለምዕራባውያን ጥቅም የቆመ ባለመሆኑ እና በምሥራቅ አፍሪካ ለውጥ ለማምጣት መሥራት መጀመሩ በአንዳንድ የውጭ ኃይሎች ዘንድ ከፍተኛ ስጋትን ፈጥሯል።
ኢትዮጵያ የቀረጸችውን የልማት አጀንዳ ለመላው አፍሪካውያን ምሳሌ የሚሆን ነው ያሉት አቶ ሙክታር፤ ምዕራባውያን ሀገራት የሚፈልጉት ደግሞ የእነሱን አጀንዳ የሚቀበልና የፖሊሲያቸው እንክብል የሚውጥ ሀገር ነው። ይህንን ለማድረግ ፈቃደኛ የማይሆን መንግሥትና ሀገር እንዲቀጥል አይፈልጉም ብለዋል።