የኢፌዴሪ የትራንስፖርት ሚኒስቴር አመራርና ሰራተኞች ለሀገር መከላከያ ሠራዊት የወር ደመዉዛቸዉን ከመስጠት በዘለለ ለማንኛዉም ሀገራዊ ጥሪም ዝግጁ መሆናቸዉን አረጋገጡ
‹‹ለሀገርን ለማዳን መቼም፣ የትም፣ በምንም እዘምታለሁ የሚለዉን ሀገራዊ ንቅናቄን ተከትሎ የኢፌዴሪ የትራንስፖርት ሚኒስቴር አመራርና ሰራተኞች በወቅታዊ ሀገራዊ ጉዳይ ላይ ሰፊ ዉይይት አድርገዋል።
መድረኩን የመሩት የትራንስፖርት ሚኒስቴር ክብርት ሚኒስትር ወ/ሮ ዳግማዊት ሞገስ ሀገራችን በአባቶቻችን መስዋዕትነት ለዘመናት ክብሯና ነጻነቷ ተጠብቆ የኖረች፣ ሰንደቅ ዓለማዋ በዓለም መድረኮች ሁሉ ከፍ ብሎ የተዉለበለበ፣ በየትኛዉም ዓለማዊ ህብረቶችና መድረኮች መስራች የሆነች ሀገር መሆኗ አዉስተዋል። ዛሬም እኛ ልጆችዋ ልክ እንደ አባቶቻችን እንዳደረጉት ሁሉ ዛሬም ልናደርግ ይገባል ብለዋል።
ክቡር ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ካሳሁን ጎፌ ቅድሚያ ለሀገር ነዉና ሀገርን የመታደግና ሉዓላዊነቷን የማስቀጠል ተልዕኮ የተጣለዉ ዛሬ ባለን በኛ ላይ ነዉ ያሉ ሲሆን ፍጹም ዴሞክራሳዊ ምርጫ ባደረግንበትና ህዳሴ ግድባችን ሁለተኛ ዙር ሙሌት በተጠናቀቀበት ማግስት ጁንታዉ የጥፋትና የሌብነት ተልዕኮዉ እየከሸፈበት በመምጣቱ የትግራዊ ህዝብ የዚህ የልማት አቅጣጫ ተጠቃሚ እንዳይሆን የመከላከያ ሃይላችንን በጀርባዉ መዉጋት ሀገርን የማፍረስ አሸባሪነቱን በተግባር ማሳየቱን አንስተዋል።
ክቡር ሚኒስትር ዴኤታ ኢ/ር የኃላእሼት ጀመረ ከዉስጥም ከዉጭም የሚሠሩ የጥፋት ሃይሎች የተለያዩ የዉሸት ዉዥንብር በመልቀቅ እርስ በርሳችን እንድንባላ በማድረግ ኢትዮጵያ የደከመች ሀገር እንድትሆን እየሠሩ መሆናቸዉን አዉቀን ከግጭት አዙሪት ወጥተን ለተለያዩ የዉሸት ወሬዎች ቦታ ሳንሰጥ እዉነቱን አዉቀን ለሌሎች በማሳወቅና ሥራችንን በአግባቡ በመስራት ልማታችንን ለማስቀጠል ከመቼዉም ጊዜ በላይ አንድነታችንን በማጠናከር ከመንግስት ጎን ልንቆም ይገባል ብለዋል።
የሚኒስቴር መ/ቤቱ አመራርና ሠራተኞችም ያለችን ሀገር አንድ ናትና ሀገርን ለመታደግ በሚደረገዉ ሀገራዊ ንቅናቄ ለመቀላቀል ስለተፈጠረዉ ዕድል አመስግነዉ ለጊዜዉ የአንድ ወር ደመዉዝ ለመስጠት በሙሉ ፈቃደኝነት የተስማሙ ሲሆን በቀጣይ ደም በመለገስ፣ በአልባሳትና በቁሳቁስ በመደገፍ እንዲሁም በማንኛዉም ጊዜ ሀገራዊ ጥሪን በመቀበል እስከ እስከ ግንባር ድረስ ለመዝመት ዝግጁ መሆናቸዉን አረጋግጠዋል።