You are currently viewing በአሸባሪው ህወሓት ትናንትም ዛሬም የተፈጸሙ ወንጀሎችን ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ አይቶ እንዳላየ እያለፈው መሆኑን የሚያጋልጡ ዘገባዎች እየወጡ ነው

በአሸባሪው ህወሓት ትናንትም ዛሬም የተፈጸሙ ወንጀሎችን ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ አይቶ እንዳላየ እያለፈው መሆኑን የሚያጋልጡ ዘገባዎች እየወጡ ነው

  • Post comments:0 Comments
በአሸባሪው ህወሓት ትናንትም ዛሬም የተፈጸሙ ወንጀሎችን ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ አይቶ እንዳላየ እያለፈው መሆኑን የሚያጋልጡ ዘገባዎች እየወጡ ነው
 
በትግራይ ክልል “ሰብአዊ ድጋፍ እናድርግ ንጹሀን ተጎዱ” በሚል ዓለም አቀፍ ጫና ሲያደርስ ቆይቶ እድሉ ያለምንም ገደብ በመንግስት የተሰጠው ዓለም አቀፍ ማህበረሰብ፤ በአሸባሪው የህወሓት ቡድን የሚፈጸሙ ግልጽ ወንጀሎችን አይቶ እንዳላየ እያለፋቸው መሆኑን የሚያጋልጡ ዘገባዎች እየወጡ ነው።
ህወሓት በደርግ ጊዜ በነበረው የትጥቅ ትግል ህጻናትን በመመልመል ለጦርነት ይጠቀም ነበር። ዛሬም ከዚህ ባህሪው አለመላቀቁን የሚያሳይ ምስል በኒዮርክ ታይምስ ዘገባ ላይ ወጥቷል።
ኒዮርክ ታይምስ ፍጹም ሚዛናዊነት የጎደለው መሆኑንና በህወሓት ፍቅር መውደቁን በሚያጋልጥ መልኩ፤ ዓለም አቀፍ ወንጀል የሆነውን ህጻናትን ለጦርነት የመመልመል ወንጀል ማጋለጡን ወደ ጎን በማለት በዘገባው ላይ ወጣቶች ህወሓትን እየተቀላቀሉ ነው የሚል ዘገባ አስነብቧል።
ለዚህ ዘገባውም የተጠቀመው ምስል አሸባሪው ድርጅት ህጻናትን ለጦርነት በግልጽ እያሰማራ መሆኑን ኒዮርክ ታይምስ መግለጽ ባይፈልግም ወንጀሉ ለዓለም ተጋልጧል።
ምዕራባዊያን ሚዲያዎች ከህወሓት ጋር ባላቸው ወዳጅነት መሬት ላይ ያለውን እውነት ከመዘገብ ይልቅ የፈጠራ ክስና ወንጀል እየሰሩ መሆናቸውን የሚያሳየው ይህ የኒዮርክ ታይምስ ዘገባ ብቻ አይደለም፤ በቅርቡ ፋይናንሻል ታይምስ የህወሓት ባለስልጣናትን ምንጭ አድርጎ በሰራው ዘገባ ላይ በሱዳን መጠለያ ውስጥ 30 ሺህ ወታደሮች እንዳሉት ገልጾ የነበረ ሲሆን፤ ጉዳዩ ከአሰበው ዓላማ ውጭ ሆኖበት ህወሓትን ሲያስወነጅልበት ሚዲያው ወታደሮች የሚለውን ቃል “ያልታጠቁ ታማኞች” በሚል ቀይሮለታል።
ለትግራይ ህዝብ ቅንጣት ታክል ርህራሄ የሌለው ይህ አሸባሪ ድርጅት በደርግ ዘመን በነበረው የትጥቅ ትግል ወቅት ለእርዳታ የመጣን እህል በመሸጥ የጦር መሳሪያ ይሸምትበት እንደነበር ዛሬ የእሱ አክቲቪስት የሆነው የያኔው የቢቢሲ የአፍሪካ ዴስክ ኤዲተር ማርቲን ፕላውት አጋልጧል።
ማርቲን ፕላውት በወቅቱ በሰራው ዘገባ በዓለም ዙሪያ ከለጋሾች ከተሰበሰበው 100 ሚሊዮን ዶላር ውስጥ 5 በመቶ የሚሆነው ብቻ ለረሀብተኞቹ ደርሷል፤ የተቀረው የህወሓት መሪዎች ለጦር መሳሪያ ግዥ አውለውታል ብሏል።
በ1977 ዓ.ም በኢትዮጵያ በተለይም በትግራይ ክልል ተፈጥሮ በነበረው ረሀብ ለተጎዱ ወገኖች ከምዕራባዊያን የተሰበሰበውን በሚሊዮን የሚቆጠር ዶላር ለተጎጂዎች ከማድረስ ይልቅ በወቅቱ የነበሩት የህወሓት አመራሮች ለጦር መሳሪያ ግዥ ማዋላቸውን ማርቲን ፕላውት በወቅቱ በሰራው ዘገባ አጋልጧል።
የህወሓት አመራር የነበሩ ግለሰብ ለማርቲን ፕላውት፤ “ገንዘቡን የምናገኘው ከእርዳታ ድርጅቶች ጋር በመደራደርና እንደነጋዴ በመቅረብ ነበር” ብለው እንደነገሩት በዘገባው ላይ ገልጿል።
ገንዘቡንም በጊዜው የነበረውን መንግስት ለመጣል ተጠቅምንበታል ማለታቸውን የጠቀሰው ማርቲን ፕላውት፤ ከምራባዊያንና ከእርዳታ ድርጅቶች የተሰበሰበውን ገንዘብ በቀጥታ ለመሳሪያ ግዥ እንዳዋሉት በዘገባው ቢያጋልጥም እንደ ቦብ ጊልዶፍ ያሉ በወቅቱ እርዳታ ያደርሱ የነበሩ ግለሰቦችና ድርጅቶች በህወሓት ላይ የቀረበውን ክስ ተከላክለውለታል።
ዛሬም ይህ ቡድን 27 አመት ስልጣን ላይ በነበረበት ወቅት ንጹህ የመጠጥ ውሃ እንኳን ለትግራይ ህዝብ ማቅረብ ሳይችል ኖሮ የግል ጥቅሙ ሲጎድልበት በትግራይ ህዝብ መሀል ገብቶ ዘረፋ እና ግድያ ላይ መሰማራቱ በተለያዩ አካላት ቢገለጽም ዓለም አሁንም ዝምታን መርጧል።
ሳምሪ በሚል ያደራጃቸው ወጣቶችና ሚሊሻዎች በማይካድራ በአማራ ብሄር ተወላጆች ላይ ቤት ለቤት በመሄድ የፈጸሙትን የዘር ማጥፋት ግድያ ዓለም አሁንም አይቶ እንዳላየ አልፎታል፤ አልሰማም እንዳይባል በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የጸጥታው ምክርቤት ላይ ንግግር ያደረጉት አምባሳደር ታዬ አፅቀ-ሥላሴ ጉዳዩን አንስተው ለአባል አገራቱ አስረድተዋል።
በቅርቡ መከላከያ ሰራዊት ከትግራይ ክልል መውጣቱን ተከትሎ በስማቸው የሚነግድባቸውን ንጹሀንን እየገደለና ሀብት ንብረታቸውን እየዘረፍ ስለመሆኑ፤ እንዲሁም በመጠለያ ያሉ ኤርትራዊያን ስደተኞችን እየጨፈጨፈ ስለመሆኑ ሪፓርቶች ቢወጡም ዓለም አይቶ እንዳላየ እያለፈው ይገኛል ሲል ኢፕድ ዘግቧል።

ምላሽ ይስጡ