ጥላቻን በጥላቻ ሳይሆን ጥላቻን በፍቅር በመቀየር አንድነታችንን አጠናክረን የኢትዮጵያን ብልጽግና ልናረጋግጥ ይገባል-ዶ/ር አለሙ ስሜ
ሰኔ 18/2013/ብልጽግና/ አገር አቀፍ የሴቶች አረንጓዴ አሻራ የችግኝ መርሃ ግብር በአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት በአዊ ብሔረሰብ አስተዳደር ዞን በባንጃ ወረዳ ተካሂዷል፡፡
በመርሃ ግብሩ ላይ በክብር እንግድነት የተገኙት በብልጽግና ፓርቲ ዋና ጽ/ቤት የፖለቲካ ፓርቲዎችና ሲቪል ማህበራት ዘርፍ ኃላፊ ዶ/ር አለሙ ስሜ ለወዳጅም ለጠላትም ትምህርት ሰጥቶ ባለፈው ስድስተኛው አገራዊ ምርጫ ማግስት አረንጓዴ በተላበሰችው በባንጃ ወረዳ የችግኝ ተከላ ማካሄዳችን ኢትዮጵያዊ አንድነታችንን ይበልጥ ያጠናክረዋል ሲሉ ተናግረዋል፡፡
ዶ/ር አለሙ አያይዘውም ጥላቻን በጥላቻ ሳይሆን በፍቅር በመቀየር አንድነታችንን አጠናክረን የኢትዮጵያን ብልጽግና ልናረጋግጥ ይገባል ያሉ ሲሆን ሁላችንም የሁላችንም መሆናችን አውቀን የክረምት ወቅት ከመግባቱ በፊት የአቅመ ደካሞችን ቤት ልንጠግንና ፍቅራችንንና አንድነታችንን በተግባር ልናሳያቸው ይገባል ሲሉ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡
የአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ዶ/ር ፋንታ ማንደፍሮ በበኩላቸው ከመላው ኢትዮጵያ ተገኝታችሁ የአንድነት አሻራችሁን ለማሳረፍ ስለመጣችሁ እያመሰገንኩ የችግኝ መርሃ ግብሩ እኛ ኢትዮጵያዊያን አንድ ስንሆን የማንወጣው ፈተና እንደሌለ ማሳያ ነው ብለዋል፡፡
በሴቶች የተደራጀ ንቅናቄ ኢትዮጵያን እናልብስ መርሃ ግብር ላይ መልዕክታቸውን ያስተላለፉት የብልጽግና ፓርቲ ሴቶች ሊግ ሊቀ መንበር ክብርት ወ/ሮ መሰረት መስቀሌ ዛሬ የምናካሂደው የችግኝ ተከላ መርሃ ግብር ኢትዮጵያ ባሸነፈችበት በስድተኛው አገራዊ ምርጫ ማግስት መካሄዱ ልዩ ያደርገዋል ሲሉ ተናግረዋል፡፡
ወ/ሮ መሰረት አያይዘውም የሴቶች የተደራጀ ተሳትፎ ጎልቶ የታየበት ስድስተኛው አገራዊ ምርጫ የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታችን አንድ እርምጃ ማደጉን ያመላከተ ነበር ያሉ ሲሆን የሴቶች ፍትሃዊ ተጠቃሚነት አሁንም በሚፈለገው ደረጃ ላይ ያልደረሰ በመሆኑ በጋራ ትግላችን ተሳታፊነታችንንና ተጠቃሚነታችንን ልናረጋግጥ ይገባል ብለዋል፡፡
ከመላው ኢትዮጵያ የተወጣጡና በችግኝ ተከላ መርሃ ግብሩ ላይ ተሳታፊ የሆኑ አካላት በእንጅባራ ከተማ በመገኘት የአቅመ ደካማ ቤቶችን ለመጠገን የሚያስችል ከሰላሳ ሺህ ብር በላይ ያሰባሰቡ ሲሆን በዶ/ር አለሙ ስሜ አማካኝነት የቤት ጥገና ስራው መጀመሩ ተገልጿል፡፡
በችግኝ ተከላ መርሃ ግብሩ ላይ በርካታ የፌዴራል፣የክልል፣የዞንና በወረዳው የሚገኙ የሃይማኖት አባቶችና የአገር ሽማግሌዎች፣የአካባቢው ነዋሪዎች፣የሴት አደረጃጀቶች እና ሌሎችም ተገኝተዋል፡፡