ድሆች እንጂ ደደቦች አይደለንም፤ አገራችንም በኛ በልጆቿ ድክመት ለጊዜው ደሃ ናት እንጂ አገርና መንግስትም፣ ስልጣኔም ምን እንደሆነ ቀደም ብሎ የገባት አገር ናት፡፡ ሉዓላዊነት፣ አልደፈር ባይነት ምን አንድሆነ ለአለም ያሳየች ለበርካቶች አርዓያ ጭምር የሆነች አገር ናት፡፡
ፍትሃዊ አስተዳደርንም ሆነ ዴሞክራሲን ቀድሞ በራሳቸው መንገድ ከተለማመዱና፣ከተገበሩና ከሰለጠኑ አባቶች ነው የተወለድነው፤ ለዚህ ደግሞ የገዳ ስርዓት ምስክራችን ነው፡፡
የነርሱ ልጆች ነን እና ስለ አገር ክብር ስለ ህዝብ አስተዳደር፤ ስለ ሰላማዊ ስልጣን ሽግግር ከማንም ሀሁ ለመማር አያሻንም፤ ባይሆን የጎደለን ለመሙላት፣ ያለንን ማበልጸግያና ማዘመኛ ጥሩ ልምድ ለመቅሰም ግን ከሁሉ ጋር እንሰራለን፡፡
ይህን ስናደርግ ግን በአንድ አለም ላይ አብረን እየኖርን እንደመሆኑ በዴሞክራሲ እናስተምራችሁና በእንርዳችሁ ስም በሶስተኛ አለም አገራት ላይ የሚፈጸመውን ደባ፤ የሚሰራ ሴራን እያየን እያጤንን ነው፡፡ በርካታ ሀገሮች በእንደዚህ አይነት ሴራ እንደፈራረሱም እያየን ነው፡፡
ይህን እያየን፤ እየሰማን *አይናችሁን ጨፍኑና እናሞኛችሁ* አያነት አካሄድን የምንቀበል የዋሆች አይደለንም፡፡
ስለዚህ ደግመን ደጋግመን የምንለው ነገር ቢኖር *የሴራና በደም የተጨማለቀ እጃችሁን ከኢትዮጵያ ላይ አንሱ*