ምርጫ 2013 ትክክለኛና እውነተኛ ምርጫ የሚካሄድበት፣ከራስ በፊት ለህዝብና ለሀገር ቅድሚያ በመስጠት ለህዝብ ሰላም ዘብ የምንቆምበት፣ምርጫው ነጻ፣ ተዓማኒና የዳበረ ዴሞክራሲ ለመገንባት በር የሚከፍት ፣በሕዝብ ውስጥ የሚብላሉ ማናቸውም ዓይነት ጥያቄዎች ለመፍታት የምንዘጋጅበት፣ አስተያየቶችና ጥቆማዎች በጥቅሉ ብሶቶችን ለማስወገድ የምንፎካከርበት ታሪካዊ ምርጫ ተደርጎ ይወሰዳል፡፡
ከህዝብ ሰላም ይልቅ ስልጣንን አስቀድመን ግርግርና ሁከት ተፈጥሮ በሰውና በንብረት ላይ ጉዳት ከመድረሱ በፊት እንደ ሰለጠነ ዜጋ በውይይት አምነን በሰላማዊ ሁኔታ ችግሮችን ለመፍታትና ምርጫው ኢትዮጵያ የምታሸንፍነት እንዲሆን የጋራ አስተሳሰብ መያዝ ያስፈልጋል፡፡
ለዚህም በመጀመሪያ ሁሉም ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች ሁሉ ቅድሚያ ለሀገርና ለህዝብ በማሰብ ወደ ሰላማዊ የፖለቲካ ተፎካካሪነት መንፈስ የመለወጥ እሳቤን ሊያዳብሩ ይገባል፡፡ ይህም ጊዜው የሚጠይቀውን ሀገራዊ አስተሳሰብና መልካም ስነ ምግባር ይዞ መገኘት ቅድሚያ የሚሰጠው ቦታ ነውና ይህን ለማድረግ የሚያስችል ልቦና ሊኖረን ይገባል፡፡
ምርጫው የሀሳብ ልዩነትነቶችን እያከበሩና ለችግሮቹ የጋራ መፍትሔ እያስቀመጡ ጠንካራ የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት ብሎም አገራዊ መግባባት የሚፈጠርበት የምርጫ ምዕራፍ አካል መሆኑን ግንዛቤ ውስጥ ማስገባት ያሻል ፡፡ስለሆነም ከቀናቶች በኋላ የሚካሄደው ስድስተኛው አገራዊና ክልላዊ ምርጫ ለሀገራችን የሚኖረው ትርጉም ከፍ ያለ ነው፡፡
ቅድመ ምርጫም ይሁን ድህረ ምርጫው ብሩህ ተስፋ የምንሰንቅበት፣ ለፀብና ለግጭት መንስዔ ከሆኑ አጓጉል ድርጊቶች ራሳችንን የምናርቅበት ፣ ከደቦ ፍርድ እና በኃይል ለማስፈፀም ትግል ከማድረግ ይልቅ ችግሮቹ ወይም ጥያቄዎቹ በሰላማዊ መንገድ የሚፈቱበትን ሁኔታ የምናመቻችበት ሊሆን ይገባዋል፡፡
በተጨማሪም የወጣቶችና የሴቶች፣የምሁራን፣የመንግስት ሰራተኞች በአጠቃላይ የህዝቡን ጥያቄዎች ከልብ በአንክሮ አዳምጦ በፍጥነት ምላሽ የሚያገኙበት፣የአገርንና የሕዝብን ሰላም የሚያናጉ፣ ለዕልቂትና ለውድመት የሚያጋልጡ ጥላቻዎች፣የስም ማጥፋት ዘመቻዎች ተወግደው ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ጎልብቶ የሚያግባቡን መፍትሔዎች የሚመነጩበት፣ በማንነትና በብሔር ጥላቻ ላይ የተመሠረቱ አውዳሚ ሐሳቦች በኢትዮጵያዊነት ጠንካራ የአንድነት ስሜት በፍቅር የሚረቱበት እንዲሆን ሁሉም የምርጫ ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች አስበው የሚሰሩበት ሊሆን ይገባል፡፡
ብልጽግና ፓርቲን ይምረጡ