You are currently viewing ቁጭ ብሎ የሰቀሉት ቆሞ ለማውርድ . . .

ቁጭ ብሎ የሰቀሉት ቆሞ ለማውርድ . . .

  • Post comments:0 Comments


/በሚራክል እውነቱ/


ኢትዮጵያ የሕዝቧን ማንነት ቁልጭ አድርገው የሚያሳዩ የበርካታ ባህልና እሴቶች ባለቤት ነች። የታሪክ መዛግብት እንደሚመሰክሩት ባህል በዕለት ተዕለት የሰው ልጆች እንቅስቃሴ፣ እርስ በእርስ የሕይወት መስተጋብር የሚፈጠር፣ ከሌሎች የምንጋራው፣ ለትውልድ የሚተላለፍ የሚተገበርና የእርስ በእርስ ጠንካራ ግንኙነትን ሊያጠናክር የሚያስችል ሰላማዊ እሴት መሆኑን ነው።


ባህልና ማህበራዊ ግንኙነትን መነጣጠል አይቻልም። አንዱ በአንዱ ውስጥ ይፈጠራል፣ ይበለፅጋል። ባህል በእርስ በእርስ ግንኙነትና መተሳሰብ ውስጥ ይገለፃል፣ ይዳብራል። በእርስ በእርስ ጠንካራ ግንኙነት ደግሞ ባህል ቅርፅ ይይዛል።

የአንድ ሕዝብ ማንነት በባህሉ ስለሚገለፅ የባህል እድገት የአገር እድገት ነፀብራቅ ይሆናል። ባህል ሲያደግ የሕዝብ ማንነት በየደረጃው እየታወቀ፣ እየጎለበተ፣ በፍቅርና በሰላም ተከባብሮ መኖርንም ያዳብራል። የአገር በጎ ገፅታም እየተገነባ ይመጣል።


ኢትዮጵያ የብዙ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች አገር በመሆኗ ብዝሀነትን ማስተናገድ የህልውናዋ ጉዳይ ነው። ይህ በመሆኑም የሕዝቦቿ ቱባ ባህል፣ የራሳቸው ቋንቋ፣ ትውፊት፣ ወግና ልማድ እንዲሁም የእምነት መገለጫ እሴቶች በሚገባ እየተስተናገደላቸው ይገኛል።

የባህሉ ባለቤቶች በገንዘብ የማይመነዘረውና የማይለካው ባህላዊ ክዋኔያቸው የሰላማቸውና የአንድነታቸው ነፀብራቅ ነውና ከፍ ብሎ እንዲሰማላቸው እንዲታይላቸውም ጭምር ይሻሉ።
ለዓለም ማህበረሰብ በማሳወቅም እሴቶቹ ይበልጥ እንዲጠነክሩና እውቅና እንዲያገኙ ለማድረግ ይታትራሉ፡፡ ይህ ምኞት እውን የሚሆነው ግን ባህላዊ ክዋኔው ባህላዊ ይዘቱን ጠብቆ በሰላም ሲከናወን ብቻ ነው።

ሰላም ለሰው ልጅ ወሳኝ መሆኑ ባያጠያይቅም የሌሎችን ባህል ሊያደንቁ ሀገር አቋርጠው የሚመጡ ቱሪስቶች ደግሞ ከምንም ነገር በላይ ሰላም ያስፈልጋቸዋል። ሰላም የሌለበት መስህብ ለማንም ምንም ትርጉም አይሰጥም። በመሆኑም እኛም ልብ ልንለውና ከምንም ነገር በላይ ልናስብበት የሚገባው ጉዳይ ለሰላማችን ቅድሚያ በመስጠቱ ላይ ሊሆን ይገባል።


ባህላዊ ቅርሶች ይዘታቸውን ጠብቀው ከትውልድ ወደ ትውልድ እንዲተላለፉ የማድረግ ኃላፊነት የሁሉም የባህሉ ባለቤት በመሆኑ ክቡሩን ባህላዊ ክዋኔ ለእኩይ ዓላማቸው ማስፈፀሚያ ሊያውሉ ከሚፈልጉ ግለሰቦችና ቡድኖች መጠንቀቅ ያሻዋል፡፡


ባህል ለሌላ ዓላማ መጠቀሚያ ሲሆን ጉዳቱ በዘመን ስሌት የሚለካ አይሆንም። ቁጭ ብሎ የሰቀሉት ቆሞ ለማውርድ እንደሚያስቸግር ሁሉ ዛሬ ላይ የምንፈጥረው የተሳሳተ መንገድ ለነገዋ ሀገራችን ጉዳቱ ከፍተኛ ነው። በመሆኑም ባህል የአፍራሽ ኃይሎች መጠቀሚያ እንዳይሆን ተገቢውን ትኩረት ልንሰጠው ይገባል፡፡


በህብር ወደ ብልጽግና !

ምላሽ ይስጡ