You are currently viewing “አገራዊ ለውጡ ከተጀመረ አንስቶ ሕዝቦችን ያራራቁ ግንቦች እየፈረሱ ናቸው” ደመቀ መኮንን ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር

“አገራዊ ለውጡ ከተጀመረ አንስቶ ሕዝቦችን ያራራቁ ግንቦች እየፈረሱ ናቸው” ደመቀ መኮንን ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር

  • Post comments:0 Comments

አገራዊ ለውጡ ከተጀመረ አንስቶ ሕዝቦችን ያራራቁ ግንቦች እየፈረሱ መሆናቸውን ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን አስታወቁ ። ኢትዮጵያ ሁሉም ዜጋ በእኩልነት የሚንቀሳቀስባትና የዜጎች ክብር የሰፈነባት፤ ሁሉም የየራሱን ማንነት በነጻነት የሚያንጸባርቅባት እንድትሆን ተግቶ መስራት እንደሚያስፈልግ አመለከቱ ።

በአገር አቀፍ ደረጃ 15ኛውን የብሔር፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን ምክንያት በማድረግ ትናንት በአዲስ አበባ በተካሄደ ውይይት ፣ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን እንዳስታወቁት ፣የለውጥ ጉዞው የኢትዮጵያ ሕዝቦች በአብሮነትና በአንድነት ወደ ብልጽግና ጎዳና እንዲሻገሩ የሚያስችል ነው።

ሁሉም ዜጋ በእኩልነት የሚንቀሳቀስባት፣ የዜጎች ክብር የሰፈነባት የተሻለች አገር እንድትሆን ተግቶ መስራት እንደሚያስፈልግ ያመለከቱት አቶ ደመቀ ፣ እያንዳንዱ ብሔር ፣ብሔረሰብ የየራሱ ቋንቋ፣ ባህልና ትውፊትና ታሪክ በነጻነት የሚስተናገዱባት ስልጡን ምድር እንድትሆን ጠንክሮ መስራት ተገቢ መሆኑን ጠቁመዋል ።

ሁሉም በወንድማማችነት፣ በመተሳሰብና አንዱ ለሌላው ጠበቃና ዋስትና በመሆን ለሕብረ ብሔራዊ አንድነቱ ዘብ እንዲቆምም ጠይቀዋል።የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባዔ አደም ፋራህ በበኩላቸው ፣ከለውጡ በኋላ በአገሪቷ በብዙ ዘርፎች እመርታዊ ለውጦች መመዝገባቸውን ገልጸዋል። ከለውጡ በፊት ከፍተኛ የዴሞክራሲ እጦት፣ ሥራ አጥነትና የሰብዓዊ መብት በሰፊው ይስተዋል እንደነበር ጠቁመዋል።ይህ ሁሉ ችግር ተደምሮ ብሔር፣ ብሔረሰቦች ለውጥ እንዲመጣ መታገላቸውንና የለውጡ አመራርም የተሻሉ ሥራዎችን በመሥራት ላይ እንደሚገኝ ገልጸዋል።

ምላሽ ይስጡ