/በሚራክል እውነቱ/
ጁንታው የህወኃት ቡድን ጉዞው ሁሉ የኋሊት ሆኗል፡፡ ትናንትም ወደ ኋላ ዛሬም ወደ ኋላ፡፡ ይህ ቡድን ለዓመታት የትርምስና የጦርነት ነጋሪት ሲጎስም ሰምተናል፡፡ አጥፊው የህወሓት ጁንታ ቡድን እርስ በእርስ እልቂት እንዲፈጠር በማድረግ ዛሬም ህዝብ በመመዝበርና የስልጣን ፍላጎትን ከህዝብ ሰላም በላይ ቅድሚያ በመስጠት ለጥፋት ሲራወጥ ይስተዋላል፡፡
ስግብግቡ የጁንታ ሀይል ለበርካታ ዓመታት ሲፈጽም የነበረው ድርጊት በህግ እንደሚያስጠይቀው ስለሚያውቅ ጨርቄን ማቄን ሳይል መቀሌ ጠቅልሎ በመግባት ምሽግ መቆፈር ከጀመረ ዓመታትን አስቆጥሯል፡፡ ወንጀል ሰርቶ ማንም ከህግ ተጠያቂነት ሊያመልጥ አይችልም፤ ይህ እውነታ ከማንም የተደበቀ አይደለምና በአጭር ጊዜ ሀገርንና ህዝብን የካዱ ህገ ወጦች በስራቸው ልክ ተመዝነው ፍርድ ማግኘታቸው አይቀርም፡፡
አሁን ባለው ተጨባጭ እውነታ ከሃዲው የህወኃት ቡድን ከሰራዊታችን የሚቃጣበትን ጥቃት መቋቋም ባለመቻሉ ማፈግፈግን መርጧል፡፡ በዚህ የመሸነፍ ስሜት ውስጥ ሆኖ ለወንጀሉ ማምለጫ ቀዳዳ ይሆናሉ የሚላቸውን አጋጣሚዎች ሁሉ በመጠቀም ላይ ነው፡፡ የእምነትና የማህበራዊ ተቋማት ደግሞ በጁንታው ለመሸሸጊያነት ተመርጠዋል፡፡ ይህ ደግሞ የፌደራል መንግስት የማህበራዊ ተቋማትና የእምነት ተቋማት አይነኩም በሚል ያስቀመጠውን አቋም እንደ አጋጣሚ በመጠቀም የለመደውን ጥፋት ለማድረስ እየተንደረደረ መሆኑን የሚያሳይ ነው፡፡
ቤተ እምነቶችን እንደ ምሽግ መጠቀም በእርግጥም የለየለት የማፊያነት ተግባርና የሐይማኖት ተቋማትን የቆሙለትን ዓላማ መዳፈር ጭምር ነው፡፡ ከቤተ እምነቱ ዓላማ ውጭ በድፍረት የጦር ካምፕ በማድረግ መሳሪያዎችን መከዘን ይህ ቡድን ለእምነት ተቋማትም ሆነ ለምዕመናኑ ያለውን ንቀት በተግባር የሚያሳይ ነው፡፡
ይህ ሀገር አፍራሹ ጁንታ ቡድን ቤተ እምነቶችን እንደ ምሽግ የተጠቀመበት ዓላማ ግልጽ ቢሆንም ዋናውና አንኳር ነጥብ ግን የመከላከያ ሰራዊት የእምነት ተቋማት ላይ ጥቃት አደረሰ በሚል ተልካሻ ምክንያት በዕምነቱ ተከታዮችን ዘንድ ድጋፍ ለማሰባሰብና ሀይሉን ለማጠናከር እንደሆነ ግልጽ ነው፡፡ ይህ ደግሞ ጁንታው የለመደው የሴራ አካሄድ ቢሆንም ህዝብ ግን ተገንዝቦታልና እቅዱ ሊሳካ ፈጽሞ አይቻለውም፡፡
ጁንታው የህውኃት ቡድን በተደጋጋሚ የሚፈጽማቸው እኩይ ተግባራት ከህገ መንግስቱ ተጻጻሪ የሆነና ግልጽ ወንጀልም ጭምር እንደሆነ በራሱ መንገድ በተግባር እያረጋገጠ ይገኛል፡፡ በሰሜን ዕዝ የሀገር መከላከያ ሰራዊት ውስጥ ሰርጎ በመግባት ሰራዊቱን በብሔራቸው በመክፈልና የትግረኛ ቋንቋ የሚናገሩትን በመለየት በዕዙ ውስጥ ስለላ እንዲያካሂዱ ኦሬንቴሽን በመስጠትና በማደራጀት ለዘመናት የክልሉን ህዝብ ሲጠብቀው የኖረው ወንድሙ ላይ ጥቃት እንዲሰነዝሩ በማድረግ ጡት ነካሽነቱን በተግባር አሳይቷል፡፡ ይህ የፈጸመው እልቂት ሳያንሰው ዛሬ ደግሞ የትግራይ ህዝብ ተዋጋልኝ ሲል ጥሪ በማስተላለፍ የእኩይነቱን ጥግ እያረጋገጠ ይገኛል፡፡
ለአገር የቆመ ሰራዊትን በማንነቱ ምክንያት ለይቶ ያስጨፈጨፈ አምባገነን ዛሬ ደግሞ በለመደው የጥፋት መንገድ የዕምነት ተቋማትን እንደ መሸሸጊያ ቢቆጥርም ከተሸሸገበት ፈንቅሎ በማውጣት ለህግ የሚቀርብ ይሆናል፡፡ የትም ቢሸሸግ ከህግ ተጠያቂነት ማምለጥ እንደማይችል፤ የፈጸመው አሳፋሪ ድርጊትም መቼም ከታሪክ ማህደር የማይፋቅ፣ በኢትዮጵያውያን ሲታወሰ የሚኖርና በታሪክም ጭምር ተሰንዶ የሚቀመጥ እኩይ ተግባር ሆኖ ይቀጥላል፡፡ ህዝብን በድሎ ህዝብ ውስጥ መሸሸግም ከሆነ ከህግ ማምለጥ አይቻልም!
ድል ለኢትዮጵያ ህዝብ!