You are currently viewing የመስከረም 30 ነገር!

የመስከረም 30 ነገር!

  • Post comments:0 Comments

ዮሐና ማርካን
አገራችን ኢትዮጵያ ባለፉት ጥቂት ዓመታት ካሳለፈቻቸው ውጣ ውረዶች አንጻር በየጊዜው በሚጎሰሙ የትርምስ ነጋሪቶች በርካቶች ዛሬስ ምን ይፈጠር ይሆን የሚል ስጋት ውስጥ እንዲገቡ አድርጓቸዋል፡፡ የሞት ቀጠሯቸው ቅዥት ሲሆንባቸው በዚህ ቀን በዚያ ቀን እያሉ የአገራችን ሰላም መሆንና የህዝቦቿ መረጋጋት ያሰከራቸው ተሸናፊዎች የሰው ህይወት ለመቅጠፍ ቀን ቀጠሮ ሲይዙ ይውላሉ፡፡
ጽንፈኝነት ክፉ ነው፡፡ ህመሙስ ቢሆን፡፡ ነቀርሳ ነው፡፡ ክፋትን፤ ጥፋትን ሲያብሰለስሉ መዋል ከራስ እድሜ ላይ ከመሽረፍና ለኪሳራ ከመዳረግ የዘለለ ጠቀሜታ የለውም፡፡ ዛሬ መስከረም ሰላሳም መንግስት የለም፤ ኢትዮጵያ አለቀላት ትፈረሳለች ሲሉ ዛሬም በአዲስ ድል ታጅበን በአዲስ መንፈስ ነጋችንን አድሰናል፡፡ የመስከረም 30 ነገር እንደተመኙልን ሳይሆን ሟርትን ወደ ሃሴት መቀየር በሚችሉ የቁርጥ ቀን ልጆች፤ አውነት፣ መተባበር፣ አብሮ መስራት አብሮ ማደግ፣ እውቀትና ትጋት ኃያልነታቸው የተገለጠበት፤ ኢትዮጵያዊነት ደምቆ የዋለበት እለት ሆኖ አልፏል፡፡
ኢትዮጵያውያን መሪያቸውን አንግሰው፤ የወንድማማችነትና የኢትዮጵያዊነት ሚዛኑን በተግባር በማሳየት ተስፋ የፈነጠቀች ፍክት ያለች ቅዳሜ መስከረም 30 እንድናሳልፍ ሆኗል፡፡ ከመዲናችን አዲስ አበባ እስከ ሐረር አገራችንን በጥበብ በመምራት ሲጨለም ብርሃን እንዳለ፣ ከዛሬ ባሻገር ብሩህ ነገ እንዳለ እያሳዩ ላሉት ለኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር አብይ አሕመድ ድጋፍ በመስጠት የጠላቶቻችን ቅስም እንዲሰበር አድርገዋል፡፡ አገራችን የትርምስ ማዕከል እንድትሆነ የሚሰራ ማንኛውም አካል እሱ ታሪክ የሚፋረደው የኢትዮጵያና የኢትዮጵያውያን ጠላት ነው፡፡ ዛሬ መስከረም 30፤ ዶ/ር አብይ እንዳሉት የተሰጠን የተፈጥሮ ጸጋ በዕወቀት እና በትጋት ከሠራንበት ምን እንደምናገኝ ያሳየን የእንጦጦ ፓርክ ፕሮጀክት በእርግጥም ነገ በልፋታችን የምናሳካው ሌላ አዲስ የድል ምዕራፍ እንዳለ ቁልጭ አድርጎ ያሳየን ነው፡፡
ዛሬ መስከረም 30 በየአካባቢ የተደረጉ የድጋፍ ሰልፎች አገራችን ወደፊት የምትሻገረው በወንድማማችነት፣ በመተባበርና በመደጋገፍ ስሜት መሆኑን በግልጽ ያሳዩ ናቸው፡፡ በተጨማሪም ከዚህ በኋላ እዚህ እና እዚያ እያማቱ፣ ህዝብ ለህዝብ እያጋጩ፣ አስታራቂ ሳይሆን ህዝብ ከህዝብ የሚያራርቅ አጀንዳ እየመዘዙ፣ በመሪ ላይ እያነሳሱ የራስን የፖለቲካ ጥማት ለማርካት የሚደረግ ማንኛውም አካሄድ የከሰረ መሆኑን ያሳዩ ናቸው፡፡ ዛሬ ትናንት አይደለም፡፡
ሚስማር ሲመታ ይጠብቃል እንዲሉ ዛሬ ሊያዳክሙን በሞከሩ ቁጥር ችግሮችን በጥበብ እያለፍን የምንበረታ፤ በከፋፈሉን ቁጥር አንድነታችንን ጠብቀን ከመቼም ጊዜ በላይ ኢትዮጵያዊነት ከፍ እንዲል የምንሰራ ህዝቦች መሆናችንን አስመስክረናል፡፡ ዛሬ የከሰሩ ፖለቲከኞች በሴራቸው የሚከፋፍሉን ሳይሆን አንድ ሆነን ወደፊት መትመመ የጀመርንበት፤ ቃላችንንም ያደስንበት ቀን ነው፡፡
ኢትዮጵያዊ ሆነው የኢትዮጵያን መፍረስ የሚመኙ፣ ከህዝብ ተፈጥረው በተከማመረ ፈተና ውስጥ እያለፈ ያለው ህዝባችን የእርስ በእርስ ትርምስ ውስጥ እንዲገባ የሚገፉ የከሰሩ ኃይሎች ዛሬ መስከረም 30 ግልጽ መልዕክት ተላልፎላቸዋል፡፡
ዶ/ር አብይ አሕመድ ዛሬ በእንጦጦ ፓርክ እንደተናገሩት አገራችንን በሁሉም መስክ የተሳካላት እስክናደርግ ድረስ በየፈርጃችን ዕረፍት ሊኖረን አይገባም፡፡ እኛ ኢትዮጵያውያን ገና ብዙ መስከረም ሰላሰዎችን በድል ታጅበን ወደፊት እንሻገራለንና በብሩህ ተስፋ በያለንበት መስክ ውጤታማ ስራ በመከወንና ልቀን በመገኘት ብልጽግናን መዳረሻው ላደረገው የለውጥ ኃይል ድጋፍ እንጂ እንቅፋት ሳንሆን በርትተን እንስራ እላለሁ ሰላም፡፡
በይቅርታ ተደምረን በፍቅር እናድጋለን፡፡ ኢትዮጵያ በልጆቿ ታፍራና ተከበራ ትኖራለች!

ምላሽ ይስጡ